በፈተና ጊዜ ቶሎ የሚታያችሁ ምንድነው?
ይህ መልእክት መዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 143
ላይ ያለውን ንጉሥ ዳዊት የገዛ ልጁ አቢሴሎም ባሳደደው ጊዜ የቃተተውን ጸሎት ይመለከታል፡፡
ወገኖቼ በጭንቅና በመከራ ጊዜ ወደ የት ትሄዳላችሁ?
ቶሎ የሚመጣላችሁ መፍትሔ ምንድነው?
ከዳዊት ሕይወት የምንማረው አንዱ ትልቅ ነገር፣ባገኘው ተግዳሮት ሁሉ በቅድሚያ ወደ አምላኩ መቃተቱን ነው፤ኃይለኛ ተማጽኖን ማደረጉን ነው፡፡በግሌ ዳዊት የሚገልጻቸው የጸሎት ቋንቋዎች ይማርኩኛል፤ልቤን እጅግ ይነኩታልም፡፡ለአብነት የተወሰኑትን ልጥቀስ፡-
ልመናዬን አድምጥ (
ቁ.1)
፣በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ (
ቁ.8)
፣ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ (
ቁ.11)
፣ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት (
ቁ.11)
፣አቤቱ ፈጥነህ ስማኝ ነፍሴ አልቃለች፤ፊትህን ከእኔ አትመልስ(
ቁ.7)
፡፡
ዳዊት የነበረበትን ሁኔታ ስናስብ፣እጅግ አስጨናቂ ጊዜ ላይ እንደ ነበረ የሚገልጸው “ነፍሴ በውስጤ አለቀብኝ፣ልቤ በውስጤ ደነገጠብኝ ” (
ቁ.4)
የሚለው አገላለጽና ጸሎት ነው፡፡ኧረ ለመሆኑ ይህ ስሜት ገጥሟችሁ ያውቃል?
እኔን በርከት ያሉ ጊዜያት ገጥሞኛል፡፡ከገጠመኝ ድንገተኛ ጫናና አስፈሪ ሁኔታ አለቀልኝ ብዬ አውቃለሁና፣በጥቂቱም ቢሆን ዳዊት ምን ዓይነት ሁኔታና ስሜት ውስጥ እንደ ነበረ ይገባኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ታዲያ በእንዲህ ዓይነት የመከራና የስቃይ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር የሚሆን ግሩም የሆነ መሸሸጊያ አላየሁም፣አላገኘሁምም፡፡ድጋፉንና
ማጽናናቱን ደጋግሜ አይቻለሁና በድፍረት ስለ ቸርነቱና ፍቅሩ ሕያው ምስክር ነኝ እላለሁ፡፡
መከራና ስቃይ ሲገጥማችሁ ምንድነው ፈጥናችሁ የምታስቡት?
ዳዊት በዚህ ጊዜ ያደረገው አንድ ነገር ብቻ ነበር፤ወደ አምላኩ መጥቶ “በጽድቅህ ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት” (
ቁ.11)
ብሎ ጮኸ!
አዎ!
ዳዊት ሰዋዊ ዘዴዎችንና መፍትሔዎችን የማያተራምስ እንደ ልቤ የተባለ የጸሎት ጀግና ነበር፡፡ሸንጋይ አካሄዶችን ሳይዘይድ፣በምሕረቱና በጸጋው ሊያነሣው የሚችለውን አምላክ የሚማጸን ልቡ በጌታው ያረፈ ሰው ነበር፡፡በግሌ በጻፋቸው መዝሙራት ሁሉ ከጌታው ጋር የተጣበቀና በአምላኩ ላይ የተደገፈ ሰው እንደ ነበር አስተውያለሁ፡፡በአምላኩ መደገፉንና መታመኑን ለመግለጽ “በእግዚአብሔር ታመንሁ፤ነፍሴን፡-እንደ ወፍ ወደ ተራሮች ተቅበዝበዢ ትሏታላችሁ?” (
መዝሙር 11
፡1)
በማለት በጽኑነት የነበረውን አቋም አሳይቷል፡፡
ወገኖቼ እናንተስ ፈተና ሲመጣ ቶሎ የሚታያችሁ ምንድነው ?
ምንድነው የምታደርጉት?
እዚህ የጠቀስሁት ምእራፍ ላይ እንደሚታየው ዳዊት ሁለት ነገሮች አድርጓል፡፡በኃይለኛ ተማፅኖ በጌታው ፊት እንደ ወደቀ የሚያሳዩ ክፍሎችን ቀድሜ አሳይቻለሁ(
ቁጥር 1
፣7
፣8
እና 11
ደግማችሁ ተመልከቷቸው)
፡፡ከዚያ በተጓዳኝ ደግሞ ቃሉንና እግዚአብሔር ቀድሞ በሕይወቱ የሠራቸውን ሥራዎች ያሰላስል ነበር(
ቁ.5)
፡፡በጥቅሉ የእግዚአብሔር ቃል “ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው” (
ሰቆ.
ኤር3
፡26)
እንደሚል በአምላኩ ላይ ተስፋውን ጣለ፡፡በፍጹም ሌሎች መፍትሔዎችንና አማራጮችን ለመፈለግ አልተቅበዘበዘም፡፡እናም በልጁ በኩል የመጣበትን መከራ ጌታ በራሱ መለኮታዊ ጥበብና መንገድ እንዴት እንዳስመለጠው እናውቃለን፡፡
እንደ ገና ልጠይቃችሁ፡፡እናንተስ በመከራና በፈተና ጊዜያት ወደ ማን ነው የምትመለከቱት?
ምን ማድረግ ነው የሚቀናችሁ?
ከብዙ ኪሳራና የሕሊና ወቀሳ ይጠብቀናልና፣በነገር ሁሉ ታማኝና የማይተወው ጌታ ላይ እራሳችንን እንጣል!
ጌታ ይርዳን!
አስደናቂው መለኮታዊው ጉብኝት
ይህን ጽሑፍ የጻፍኩት ሉቃስ 24፡13-53 ያለውን ክፍል ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ይህ ክፍል ከኢየሩሳሌም 11 ኪሎ ሜትር ወደሚርቀው ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይጓዙ የነበሩት ቀለዮጳና ባልደረባው፣ስለደረሰባቸው የሕይወት መጠውለግና ከዚያም ያገኛቸውን ሰማያዊ ብርታትና መነቃቃት የሚተርክ ክፍል ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እንደ ዝናብ በልባቸው ላይ ያለ ማቋረጥ ለሦስት ዓመት ሲዘራ ነበር የከረመው፡፡ቢሆንም ወደ ልባቸው ሲወረወር የነበረው ያ ትምሕርት በማስተዋል አልታገዘምና፣በእምነት ከሕይወታቸው ጋር አልተዋሃደምና ለጊዜው አልጠቀማቸውም ማለት ይቻላል፡፡የኢየሱስ የእረኛቸው ያ አሳዛኝ ስቃይ፣እንግልትና ሞት(አስቀድሞ ቢያሳስባቸውም)ሲከሰት፣ሕይወታቸው ተናጋ፣ተቃወሰ፤ሁለንተናቸው በተስፋ መቁረጥ ጉም ተሸፈነ፡፡ከዚህም የተነሣ በብዙ ኀዘን ውስጥ ሆነው፣ወደ ቀድሞ መንደራቸው ሕይወትን ከዚሮ ለመጀመር ይጓዙ እንደ ነበር ክፍሉ ይጠቁማል፡፡
እምነታቸውና ተስፋቸው እየጠወለገ ስለነበር፣እርስ በርስ የሚነጋገሩት ከተሸነፈና ካበቃለት ሰው የሚወጣ ቋንቋ ነበር፡፡ቢሆንም ጌታችን ኢየሱስ የትንሣኤ አምላክ ነውና፣ሕይወታቸውን እንደገና በብርሃን ሊሞላው በድንቅ ተገለጠ፡፡ከነሱ ጋር ሰማያዊ አጀንዳ ነበረውና፣ “እሱ ራሱ ቀርቦ ከነርሱ ጋር ይሄድ ነበር” (ቁ.15)፡፡በመንገድ እያወራቸው ሳለ ልባቸው በመንፈስ ቅዱስ ጉብኝት እየተቃጠለ ነበር የሚጓዙት(ቁ.32)፤እሱ ሲገኝና ሲገለጥ ሁሌም ልዩ ነውና፤ልዩነት ይፈጠራልና!
በነገራችን ላይ እነዚህን ሁለት ሰዎች ለዚህ ዓይነቱ የሕይወት መጠውለግና ውድቀት የዳረጓቸው ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ነበሩ፡፡ይህንን አስመልክቶ ኢየሱስ ተግሣጽ በሞላበት ጥያቄ እንዲህ ነበር ያላቸው፡-
“እናንተ የማታስተውሉ ነቢያትም የተናገሩትን ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ክርስቶስ ይህንን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን?” (ቁ.25)
ባጭሩ የነገራቸውን አለማስተዋልና ልባቸው ለማመን መዘግየቱ ነበሩ መንፈሳዊ ችግሮቻቸው፡፡ኢየሱስ የነበሩበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ያውቅ ስለ ነበር፣“ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው” (ቁ.27)፡፡ በማዕድ ላይ አብረው ሳሉ እንጀራን ቆርሶ ሲሰጣቸው “ዓይናቸው ተከፈተ አወቁትም(relational knowledge)” (ቁ.31፤አጽንኦት የኔ)፡፡ታዲያ ከዚህ ድንቅ ጉብኝት በኋላ የተፈጠረው አስደናቂ ነገር ይኼ ነበር፡፡ወዲያው በአዲስ ጉልበትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የትንሣኤው ምስክር ሊሆኑ በቅተዋል(ቁ.33-35)፡፡እጅግ የሚገርምና አስደናቂ ለውጥ ነበር፡፡ይኼ ወደ ኢየሩሳሌም የመመለስ ድፍረትና ኃይል የመጣው፣ልባቸው ላይ በተካሄደው መንፈሳዊ ለውጥ ምክንያት መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፤የሰው ልጅ ዓይኑ ሲበራ እንዲህ ነው የሚሆነውና!
በግሌ ከብዙ ዓመታት በፊት፣ኢየሱስ በድንቅ ሁኔታ ተገልጦላት የነበረች አንድ ክርስትያን፣በምትሠራበት መሥሪያ ቤት ላገኘችው ሁሉ ስለ ኢየሱስ ትመሰክር እንደ ነበር ትዝ ይለኛል፡፡ከነበራት ሙያዊ ክብር ወርዳ ለሊስትሮና ለጥበቃ ሳይቀር የጌታን አዳኝነት ስትመሰክር ላያት ሰው ያበደች ትመስል ነበር፡፡ብዙዎችም ተሰናክለውባት እንደ ነበር ትዝ ይለኛል፡፡አዎ!የአርያም ባውዛ ልብ ላይ በድንቅ ሲበራ፣አስደናቂ ነው፤ከአእምሮ በላይ ነው፤ልዩ ነው!
እነዚህ ሁለት ሰዎች ይህንን የትንሣኤ አምላክ ከወትሮው በተለየ መልኩ በማወቃቸው ሕይወታቸው በእምነትና በተስፋ አሸበረቀ፡፡ስለዚህም በብዙ ደስታ ከባልደረቦቻቸው ጋር ተቀላቀሉ፡፡ባነበብኩት ቁጥር የሚገርመኝ አስደናቂ ታሪክ! የአርያም ነፋስ ልባችንን ሲያገኘውና ሲነካን፣እየጠወለገ ያለው የብዙዎቻችን ሕይወት እንደዚሁ ነው የሚሆነው፡፡ዓይኖቻችን ተከፍተው የጌታን ክብር በጭላንጭሉ ብናይ ነገሮች በብዙ መልኩ ይቀየራሉ፡፡
ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በኤፌሶን ምእራፍ አንድ ላይ በክርስቶስ የሆነላቸውን ነገር ሰፋ ባለ ሁኔታ እስከ ቁ.11 ድረስ ከዘረዘረና ካስረዳቸው በኋላ፣የጥበብና የመገለጥ መንፈስ እንዲሰጣቸው እንደሚጸልይላቸው የነገራቸው(ቁ 16)፡፡በግሌ በክርስትና ሕይወቴ ከዚህ ሌላ በቅድሚያ የሚጸልበት ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡በጽሑፉም ሐዋርያው ጳውሎስ የጥበብና የመገለጥ መንፈስ ሲኖራቸው፣ የልብ ዓይኖቻቸው እንደሚበሩ ነግሯቸዋል(ቁ.18)፤የልባቸው ዓይኖች ሲበሩ ደግሞ ለምን እንደተጠሩ፣በቅዱሳን መካከል ያላቸውን የርስት ክብርና የትንሣኤውን ኃይል እንደሚያውቁ ገልጾላቸዋል(ቁ.19)፡፡
ወገኖቼ የልባችን ዓይኖች ሲበሩ፣በመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚመጣው ለውጥ እንደ ቀላል መታሰብ የለበትም፡፡አዎ!መንፈሳዊ ዓይኖቻችን ሲበሩ ከመጠውለግና ከተስፋ መቁረጥ በድንቅ ሁኔታ እንወጣለን፡፡እምነታችን ያድጋል፣ይጠነክራል፤ብሎም የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን ይለቀቃል(ሮሜ 5፡2)፡፡ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መጽሐፍ “ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤አሜን!” (ሮሜ 16፡26-27) እንደሚል ድካም በብርታት ይቀየራል!
የትንሣኤው ኃይል
ከመጠውለግ ያወጣል
ወደ ኢየሩሳሌም ይመልሳል!