በፈተና ጊዜ ቶሎ የሚታያችሁ ምንድነው?
ይህ መልእክት መዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 143 ላይ ያለውን ንጉሥ ዳዊት የገዛ ልጁ አቢሴሎም ባሳደደው ጊዜ የቃተተውን ጸሎት ይመለከታል፡፡
ወገኖቼ በጭንቅና በመከራ ጊዜ ወደ የት ትሄዳላችሁ? ቶሎ የሚመጣላችሁ መፍትሔ ምንድነው? ከዳዊት ሕይወት የምንማረው አንዱ ትልቅ ነገር፣ባገኘው ተግዳሮት ሁሉ በቅድሚያ ወደ አምላኩ መቃተቱን ነው፤ኃይለኛ ተማጽኖን ማደረጉን ነው፡፡በግሌ ዳዊት የሚገልጻቸው የጸሎት ቋንቋዎች ይማርኩኛል፤ልቤን እጅግ ይነኩታልም፡፡ለአብነት የተወሰኑትን ልጥቀስ፡-
ልመናዬን አድምጥ (ቁ.1)፣በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ (ቁ.8)፣ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ (ቁ.11)፣ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት (ቁ.11)፣አቤቱ ፈጥነህ ስማኝ ነፍሴ አልቃለች፤ፊትህን ከእኔ አትመልስ(ቁ.7)፡፡
ዳዊት የነበረበትን ሁኔታ ስናስብ፣እጅግ አስጨናቂ ጊዜ ላይ እንደ ነበረ የሚገልጸው “ነፍሴ በውስጤ አለቀብኝ፣ልቤ በውስጤ ደነገጠብኝ ” (ቁ.4) የሚለው አገላለጽና ጸሎት ነው፡፡ኧረ ለመሆኑ ይህ ስሜት ገጥሟችሁ ያውቃል? እኔን በርከት ያሉ ጊዜያት ገጥሞኛል፡፡ከገጠመኝ ድንገተኛ ጫናና አስፈሪ ሁኔታ አለቀልኝ ብዬ አውቃለሁና፣በጥቂቱም ቢሆን ዳዊት ምን ዓይነት ሁኔታና ስሜት ውስጥ እንደ ነበረ ይገባኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ታዲያ በእንዲህ ዓይነት የመከራና የስቃይ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር የሚሆን ግሩም የሆነ መሸሸጊያ አላየሁም፣አላገኘሁምም፡፡ድጋፉንና ማጽናናቱን ደጋግሜ አይቻለሁና በድፍረት ስለ ቸርነቱና ፍቅሩ ሕያው ምስክር ነኝ እላለሁ፡፡
መከራና ስቃይ ሲገጥማችሁ ምንድነው ፈጥናችሁ የምታስቡት? ዳዊት በዚህ ጊዜ ያደረገው አንድ ነገር ብቻ ነበር፤ወደ አምላኩ መጥቶ “በጽድቅህ ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት” (ቁ.11) ብሎ ጮኸ! አዎ! ዳዊት ሰዋዊ ዘዴዎችንና መፍትሔዎችን የማያተራምስ እንደ ልቤ የተባለ የጸሎት ጀግና ነበር፡፡ሸንጋይ አካሄዶችን ሳይዘይድ፣በምሕረቱና በጸጋው ሊያነሣው የሚችለውን አምላክ የሚማጸን ልቡ በጌታው ያረፈ ሰው ነበር፡፡በግሌ በጻፋቸው መዝሙራት ሁሉ ከጌታው ጋር የተጣበቀና በአምላኩ ላይ የተደገፈ ሰው እንደ ነበር አስተውያለሁ፡፡በአምላኩ መደገፉንና መታመኑን ለመግለጽ “በእግዚአብሔር ታመንሁ፤ነፍሴን፡-እንደ ወፍ ወደ ተራሮች ተቅበዝበዢ ትሏታላችሁ?” (መዝሙር 11፡1) በማለት በጽኑነት የነበረውን አቋም አሳይቷል፡፡
ወገኖቼ እናንተስ ፈተና ሲመጣ ቶሎ የሚታያችሁ ምንድነው ? ምንድነው የምታደርጉት? እዚህ የጠቀስሁት ምእራፍ ላይ እንደሚታየው ዳዊት ሁለት ነገሮች አድርጓል፡፡በኃይለኛ ተማፅኖ በጌታው ፊት እንደ ወደቀ የሚያሳዩ ክፍሎችን ቀድሜ አሳይቻለሁ(ቁጥር 1፣7፣8 እና 11 ደግማችሁ ተመልከቷቸው)፡፡ከዚያ በተጓዳኝ ደግሞ ቃሉንና እግዚአብሔር ቀድሞ በሕይወቱ የሠራቸውን ሥራዎች ያሰላስል ነበር(ቁ.5)፡፡በጥቅሉ የእግዚአብሔር ቃል “ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው” (ሰቆ.ኤር3፡26) እንደሚል በአምላኩ ላይ ተስፋውን ጣለ፡፡በፍጹም ሌሎች መፍትሔዎችንና አማራጮችን ለመፈለግ አልተቅበዘበዘም፡፡እናም በልጁ በኩል የመጣበትን መከራ ጌታ በራሱ መለኮታዊ ጥበብና መንገድ እንዴት እንዳስመለጠው እናውቃለን፡፡
እንደ ገና ልጠይቃችሁ፡፡እናንተስ በመከራና በፈተና ጊዜያት ወደ ማን ነው የምትመለከቱት? ምን ማድረግ ነው የሚቀናችሁ? ከብዙ ኪሳራና የሕሊና ወቀሳ ይጠብቀናልና፣በነገር ሁሉ ታማኝና የማይተወው ጌታ ላይ እራሳችንን እንጣል!
ጌታ ይርዳን!
No comments:
Post a Comment