በእግዚአብሔር መደሰት(Enjoying
God )
በዚህ ዓለም ከፍ ያለውና ተወዳዳሪ የሌለው ነገር በእግዚአብሔር መደሰት ነው፡፡ሰዎች በብዙ ነገር ደስታን ለማግኘት ይጥራሉ፡፡እነዚህ ደስታን ይሰጣሉ የሚባሉት ነገሮች ግን ዘለቄታዊ ርካታ ያለው ደስታ የሚሰጡ ሳይሆን፣ከሰዓታት በኋላ እንደ ንፋስ የሚተን ደስታን ነው የሚሰጡት፡፡ይህንን በራሴ ሕይወት ከሱስና ከዝሙት ጋር በተያያዘ አይቼዋለሁና መላምት አይደለም የምናገረው፡፡ለዚህም ነው በአይሁድ የዳስ በአል ማብቂያ ላይ “ኢየሱስ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ” (ዮሐንስ 7:37) ብሎ የጮኸው፡፡ለብዙ ቀናት ሲጠግብና ሲንበሸበሽ የሰነበተን ሰው እንዲህ አይነት ግብዣ መጠየቅ ቀልድ ነው የሚመስለው፤ነገር ግን እጅግ መሠረታዊ ጥያቄ እና ግብዣ ነበር፡፡ያ አይሁዶች የነበሩበት ግብዣ ሥጋና ነፍስ ድረስ ሊደርስ የሚችል ጊዜያዊ ደስታን ፈጥሮ ሊሆን ይችላል፤ነገር ግን ወደ ውስጥ ዘልቆ በፍጹም መንፈስን ሊያገኝ አይችልም ነበር፡፡ለዚህ ነው በእንደዚህ ዓይነት ፈንጠዝያዎች፣ደስታችን ሙሉ ሊሆን የማይችለው፡፡ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ከእንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ደክሞን በባዶነት የምንመለሰው፡፡በእግዚአብሔር መደሰትን የሚተካከለው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም መንፈሳችን ከመንፈሱ ጋር ሕብረት ስለሚያደርግ፣ጥልቅ የሆነ፣ ዘለቄታ ያለውና እየጨመረ የሚሄድ ደስታ ነው የምናገኘው፡፡ወደ ቤትም ስንመለስ እየዘመርንና እየተቀጣጠልን ነው የምንመለሰው፡፡አንዳንዴም ከደስታችን ብዛት፣መተኛትም ላያምረን ይችላል፡፡
በእግዚአብሔር የመደሰታችን መጠን እሱን እንደ መቅረባችን፣እንደ እምነታችንና እርሱን እንደማወቃችን ይወሰናል፡፡አዎ በእግዚአብሔር እና በአግዚአብሔር ሕልውና ውስጥ ሆኖ ለመደሰት እና ለመርካት እግዚአብሔርን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡በተለይ ፍቅሩን መረዳት ይፈልጋል፤ቃሉ “የእናንተ ስርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ” (ኤፌሶን 3፡18-19) ይላልና፡፡አዎ!በእግዚአብሔር መደሰታችን እሱን በማወቃችን ልክ እያደገ የሚሄድ እንደሆነ ልብ እንበል፡፡በዚሁ በተጠቀሰው ምንባብ ላይ “የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ” የሚለው ሐሳብ በቀለም ደረጃ ስለሚታወቅ ዕውቀት ሳይሆን በጠለቀ ሕብረት(deeper intimacy) ስለሚገኝ መረዳት፤መገለጥ እና ማወቅ ነው የሚናገረው፡፡ሕብረታችን ደግሞ ከቃሉ ጋር በምናደርገው መጣበቅ እና በጸሎት በምናሳልፋቸው ጊዜዎች እየጠበቀ ይመጣል፡፡እንደዚህ ያለመታከት ስንገፋ ነው እያወቅነው፣እየተገለጠልን፣መንፈሳዊውን ዓለም እየተረዳንና ለእኛ ያለውን የክርስቶስን ፍቅርና አላማ እያስተዋልን የምንመጣው፡፡
ይህንን መርሕ ሁልጊዜ ልብ እንበል፡፡በመንፈሳዊው ዓለም መገለጥ (revelation) ሁልጊዜ ደስታ (joy) አለው፡፡ጌታን ባወቅነው እና በተረዳነው መጠን እምነታችን እያደገ ስለሚመጣ፣ዕረፍታችንና (እብ 4፡11) ደስታችን እየጨመረ ይሄዳል፡፡የእግዚአብሔር ቃል እምነት ወደ እግዚአብሔር ደስታ ውስጥ የሚከተን ቁልፍ ነገር እንደ ሆነ ሲገልጽ “የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ” (ሮሜ 15፡13) ብሎ ይናገራል፡፡አዎ በእምነት መቆማችንና መመላለሳችን፣የደስታ እና የሰላም መንፈስ እንድንሞላ ዋና በር እንደ ሆነ ነው የሚያበስረን፡፡ቃሉ የእምነትን አስፈላጊነትን ሲገልጽ“በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል”(ሮሜ 5፡2) ይላል፡፡እዚህ ጋ ሊታወቁ የሚገባቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡እምነትን የምናገኘውና እምነታችን የሚያድገው መንፈስ የሆነውን ቃል ስንሰማ ነው ቃሉ “እምነት ከመስማት ነው” ሮሜ 10፡17) ይላልና፡፡ወደ እግዚአብሔር ሕልውናና ማለቂያ ወደሌለው ጸጋ ውስጥ የምንገባው ደግሞ፣ቃሉ በእምነት ከሕይወታችን ጋር ሲዋሃድ ነው፡፡፡፡ስለዚህ ከእኛ በኩል ትልቅ ኀላፊነት እንዳለ ሊመሠመርበት ይገባል-ከምንጩ ጋር በሚገባ መተከልና መትጋት፡፡
ጠላት የሚተጋው ከጌታ ጋር ያለን ሕብረት ላይ ላዩን እንዲሆን እና ወደ ጠለቀ ነገር እንዳንሄድ በማዋከብ እና በሌሎች ነገሮች አእምሮአችንን እየከፋፈለ በማራቆት ነው፡፡እዚህ ጋ በማስተዋል የምንወስደው ርምጃ እጅግ ይጠቅመናል፡፡ማለትም ጸንተንም የክፉን ሐሳብ በኃይል መቃወም ይኖርብናል፡፡እንዲህ የምላችሁ ለምን መሰላችሁ? ብዙ ጊዜ በማስተዋል ጸንቼ የጠላትን ሥራ ሳፈርስ፣ጌታ የሚደንቅ ነገር ውስጥ ሲከተኝ ስላየሁኝ ነው፡፡በድጋሚ እላለሁ፣የጠላትን ከበባ ለማሸነፍ መንቃትና መዋጋት ይኖርብናል፡፡ንቁና ትጉ የሚሉት ትእዛዞች ተደጋግመው በቃሉ ውስጥ ይገኛሉና!
በእግዚአብሔር ለመደሰት ምን እናድርግ የሚለው ላይ አጭር ተግባራዊ ነገር አስቀምጬ ጽሑፌን ልቋጭ፡፡የምናደርገው አንድ ነገር ብቻ ነው፡-ከጌታ ጋር በቂ ጊዜ ወስደን ሕብረት ማደረግ! ሌሎቹ ርምጃዎች እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡መዘርዘር ካስፈለገ፣የሚከተሉትን እናድርግ፡-
1.ከጌታ ጋር ተስማምተን ባልሄድንባቸው ነገሮችን ላይ ከምር የሆነ፣እውነተኛና ጥልቅ ንስሐን እንግባ፤ምክንያቱም እውነተኛ ንስሐ ያድሳልና ነው፡፡ይህንን ርምጃ ከወሰድን በኋላ ከኃጢያት ወቀሳ ለመውጣት በእምነት እንቁም(ጌታ መሐሪና ይቅር ባይ ነውና!)
2.ቃሉ ውስጣችንን እንዲለውጠውና ልባችንን የእግዚአብሔር ሰላምና ደስታ እንዲያገኘው ከፈለግን፣እናጥናው፣ያለ ማቋረጥ እናሰላስለው ደግሞም እንተግብረው
3.ጠንከር ያሉ ጸሎቶችን እንጸልይ፤በጊዜውም አለጊዜውም ፊቱን ያለ ማቋረጥ እንፈልግ
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች በማድረግ ብዙ መጽናናትን፣ደስታን፣ዕረፍትን እና በረከትን አግኝቻለሁ፡፡እንደሚረዳ፣እንደሚደግፍ፣እንደሚያጽናና ደስታን እንደሚያጎናጽፍ ሕያው ምስክር ነኝና፣በሚገባ እንድትተጉና ጌታን እንድታዩት አደፋፍራችኋለሁ፡፡እርሱ ታማኝ ነው፤እርሱን የሚመስል የለም፤ስለዚህ ኑና በሕልውናው ውስጥ ዕረፉ!!