Wednesday, September 18, 2013

እግዚአብሔር ይናገራል





እግዚአብሔር ይናገራል


ቃሉን በማሰላሰል፣በማጥናትና በሚገባ በመጸለይ መንፈሳችንን ንቁ ካደረግንእግዚአብሔር ድምጹን ያሰማናል፡፡የእግዚአብሔር ድምፅ ወደ እኛ በዓላማ ይመጣል፡፡የእግዚአብሔር ድምጽ ሊያነቃን፣ከድንዛዜ ሊያወጣን፣አቅጣጫ ሊያሳየን ወይም ሊያስቀይረንተስፋ ሊሰጠን፣እንደማይተወን ሊገልጽልንና ከፍ ያለ ተልእኮ ሲኖር ይመጣል፡፡

የእግዚአብሔር ድምፅ ወደ ሕይወታችን ሲመጣ ብዙ ለውጦች ይከሰታሉ፡፡በዚህ ዙሪያ መዝ 294-11 ላይ ያለውን ክፍል መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡እዚህ ክፍል ላይ ስለ እግዚአብሔር ድምጽ የሚደንቁ አገላለጾችን እናገኛለን፡፡በመግቢያ ላይ የእግዚአብሔር ድምጽ በታላቅ ክብር ነው” ብሎ ይናገራል፡፡ይህ አገላለጽ አዘውትረን ከምንሰማቸው ድምጾች የእግዚአብሔር ድምጽ ለየት ያለ እንደ ሆነ ነው የሚጠቁመን፡፡በዚሁ ምእራፍ ወረድ ብሎ እንደ ተገለጸው፣የእግዚአብሔር ድምጽ ወደ እኛ ሲመጣ አልቻል ያለን፣ያስቸገረን ነገር ሁሉ ይሰብራል፣ደካሞችን በኃይል እንዲበረቱ ያደረጋል፣ወደ እኛ የሚመጣን የእሳት ነበልባል ይቆርጣል፣በሰላም ይባርከናል፣ኃይል ይሰጠናል፣ያጠነክረናል፣የተሰወረን ነገር ይገልጣል ወዘተ፡፡

በእንባቆ 21-2 የእግዚአብሔር ድምፅን እንዴት መስማት እንደምንችል እና ማድረግ ስላለብን ነገሮች ጥሩ መርሕ አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ቃሉ እንዲህ ይላል፡-
በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ በአምባ ላይም እወጣለሁ የሚናገረኝንም ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ፡፡እግዚአብሔርም መለሰልኝ እንዲህም አለ፡-አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ በጽላትም ላይ ግለጠው
ይህንን ክፍል መሠረት በማድረግ ሦስት የጸሎት መርሖዎችን ማውጣት ይቻላል፡፡መርሖዎቹንም እንደሚከተለው አስቀምጫቸዋለሁ፡-
  • በመጠበቂያችን ላይ መቆም-ይህ የሚያሳየው በጸሎትና በጸጥታ ጌታን እየጠበቅን በፊቱ መሆን እንዳለብን ነው
  • የሚናገረኝንም ስለ ክርክሬም……-እግዚአብሔር በጸሎትና በጸጥታ መንፈሳችንን አንቅተን ስንጠብቅ ይናገራል
  • ራእዩን ጻፍ በጽላትም ግለጠው -እግዚአብሔር የተናገረንን ነገሮችና ያየናቸውን ራእዮች ወዲያውኑ በጽሑፍ ማስፈር፣የምንጸልይባቸውን ነገሮች በጥራት በቀጣይነት እንድንጸልይባቸውና መልስም ሲመጣም ለምስጋናም ይመቸናልና ነው፡፡

የእግዚአብሔር ድምጽ ሲመጣ ብዙ ጊዜ ሁለት መልኮች አሉት፡፡በተለይ በጸሎት ሆነን ሳለ -

  • ድንገትነት(spontaneity) ባለው ሁኔታ ይመጣል
  • ለየት ያሉ ፈጽሞም ያልጠበቅናቸው ሐሳቦች ብቅ ይላሉ(unique unexpected thoughts)

አዎ! እግዚአብሔርማ ይናገራል፡፡ያልተናገረበት ጊዜ የለም፡፡ችግሩ ያለው የኛ ጆሮና ልብ ጋ ነው እንጂ!የእግዚአብሔር ድምጽ ወደ ሕይወታችን እንዳይመጣ እንዳይባርከንና ሩጫችን እንዳይፈጥን የሚከለክሉ ብዙ ሁኔታዎች አሉ፡፡ከነዚህ ለምሳሌ በእግዚአብሔር ፊት በቂ ጊዜ አለመቆየት፣ቃሉን አለማጥናትና አለማሰላሰል፣በሕይወታችን አቅፈን የያዝናቸው ኃጢአቶች ሲኖር  እና አለመታዘዝ ሲበዛ፣አለማመንና አለመጠባበቅ(ኢሳይያስ 42፡20) በዋናነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

እግዚአብሔር አልሰማ እያልን ስናስቸግረው፣ በተለያዩ ከባድ የሕይወት ሁኔታዎች ውስጥ ሊያሳልፈን ይችላል፡፡ሲ.ኤስ ሉዊስ የሚባሉ የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔር በመከራችንና በሕመማችን ጊዜ የሚናገረን ነገር በቀላሉ ይሰማናል ብለዋል፡፡የእግዚአብሔር ቃል እስራኤላውያን አልሰማ እያሉ ሲያስቸግሩት እንዲህ ብሎ ተናግሯል፡-


“ስለዚህ እነሆ አባብላታለሁ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ ለልብዋም እናገራለሁ(ሆሴዕ 26) 



ወረድ ብሎ ባሉ ጥቅሶች ላይ ለልባቸው ከተናገራቸው በኋላ ስለሚያገኙት በረከት በሚደንቅ ሁኔታ ተዘርዝሯል፡፡በቅድሚያ ‹‹እንደ ህጻንነት ወራት ትዘምራለች›› (ቁ.17)የሚል በረከት ተጠቅሷል፡፡ይህም ማለት እግዚአብሔር ሲናገረን ኃይላችን እንደሚታደስ፣ውስጣችን በሰላምና በደስታ እንደሚሞላና ተስፋችን እንደሚጨምር ነው የሚያሳየን፡፡እዚህ ሆሴዕ ባለው ክፍል ላይ ‹‹ስለዚህ›› የሚለው ቃል ምእራፍ ሁለት ላይ ያለውን ሐሳብ ለማገናኘት ጸሐፊው የተጠቀመበት (እስራኤል በሴት ጾታ ተጠቅሳለች) ሲሆን እግዚአብሔር ከኃጢአቷ እንድትመለስ ደጋግሞ ቢናገራት አልሰማ ስላለች ነው ወደ ምድረ በዳ ሊወስዳት የፈለገው፡፡በእኛም ሕይወት እንዲሁ ነው የሚሆነው፡፡ምንም እንኳ የሚሻለውና ከፍ ያለው ሐሳቡ ሳናስቸግረውና አስቀድመን ድምጹን ሰምተን ወደ አሰበልን ፍጻሜ እንዲመራን ልባችንን እና ሁለንተናችንን ብንሰጠው ቢሆንም፣እግዚአብሔር እኛን ከጥፋትና ከጉስቁልና ለመመለስ በተለያዩ አጣብቂኞች ውስጥ ሊያሳልፈን ግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡

እግዚብአብሔር ድምጽህን ሰምተን እንድንታዘዝህ ጆሮዎቻችንን ክፈትልን!
ማስተዋልን ስጠን!


















No comments:

Post a Comment