የምጥ ጸሎት በተግባር ደረጃ
የምጥ ጸሎት አስደናቂ ነው፡፡ይህን
ጸሎት እንድለማመድ አጋጣሚውን የፈጠሩልኝ በተለያዩ ጊዜያት በክርስትና ዘመኔ የገጠሙኝ ስብራቶች ናቸው፡፡በነዚያ ስብራት ጊዜዎች
የምጥ ጸሎትን መለማመድ ጀመርኩ፡፡አደርግ የነበረው በገጠሙኝ ስብራቶች ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ነጻ እስክሆን የመንፈስ መለቀቅ እስኪመጣ
ድረስ በጸሎት ውስጥ እቆይ ነበር፤አምጥም ነበር፡፡ስለዚህም ብዙ በረከት አግኝቼበታለሁ፤የጌታንም ክንድ አይቼበታለሁ፡፡
ማቴ 6፡6 ላይ
የምናገኘው ቃል ለጸሎት ትልቅ መርህ ያለው ቃል ነው፡፡እንዲህ ይላል፡-‹‹አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝ ግባ መዝጊያን
ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤በስውር የሚያይ አባትህ በግልጽ ይከፍልሀል፡፡››እልፍኛችን (our closet) ውስጥ
ስናምጥና ስንቃትት የሚመጣ በረከት አለ፡፡‹‹በግልጽ ይከፍልሀል›› የሚለው ቃል በጣም ያስደንቀኛል፡፡ክፍያው ምን መሰላችሁ፡-
- በስውር የሚያይህን አባታችንን በመንፈስ ማየት እንጀምራን
- ምህረት፣ጸጋ ፣ደስታ ወዘተ ወደ ህይወታችን ይመጣሉ
- የምንጸልይበት ጉዳይም መልስ ያገኛል
- ከወትሮው ለየት ያለ ቀንበርን የሚሰብር ቅባት ወደ ህይወታችን ይመጣል ወዘተ
ኢሳያስ 66፡5-9 ላይ በምጥ
ጸሎት የሚወለዱ ነገሮች እንዳሉ እናያለን ፡፡ቃሉ እንዲህ ይላል፡-‹‹ጽዮን እንዳማጠች ልጆችን ወልዳለችና በውኑ ወደ መውለድ
የማደርስ እኔ አላስወልድምን ? የማስወልድስ ማህጸንን እኔ እዘጋለሁን ? በዚህ ቃል የምንረዳው ነገር ከብዙ ምጥ በኋላ
የመውለድ ጊዜ እንዳለ ነው የምንገነዘበው፡፡በምጥ ጸሎት ብዙ ነገሮች ሲወለዱ አይቻለሁ፡፡በዚህ ዘመን ለቤተ ክርስትያን መታደስ
የትውልዱ ሸክም ያላቸው ሰፊ ራእይ ያረገዙ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡በዚህ ቃል ላይ እኔ
ራእይ ሰጥቼ ወደ ፍጻሜ አላመጣውምን እያለ ነው እግዚአብሄር የሚጠይቀን፡፡በእርግጥ እኛ ከስስት የራቀ የመንግስት ሀሳብ ይውረሰን
እንጂ እግዚአብሄር ነገሮችን በጊዜው ውብ አድርጎ ያሳየናል፡፡ታማኝ ነው፡፡
ስለዚህ ይህንን ጸሎት ለመጸለይ፡-
- የከበደንን የህይወት ሁኔታ ስም ሰጥተነው ወደ ጌታ እንቅረብ(let us be specific)
- ለጸሎት የሚመች ቦታ መርጠን ክፍላችንን እንዝጋ(ሞባይል እና ኮምፒዩተር እናጥፋ ቢቻል)
- ጸሎትን ብዙ ጊዜ በስጋ ስለምንጀምረው የሚሰማን ነገር ባይኖር እንኳ በእምነት ከጸሎት ቦታችን ሳንነሳ በጽናት ረዘም ላለ ጊዜ እንቀጥል
- መንፈስ ቅዱስ እንደሚመራን ለመሆን መንፈሳችንን እናንቃ፡-ማልቀስ ካለብን እናልቅስ፤መዘመር ካለብን እንዘምር ወዘተ
- በመሃል አይምሮአችንን የሚከፋፍል እና ጸሎት ላይ ትኩረት ለማድረግ ካቃተን በሐይል እየተቃወምን እንጸልይ
- ለረጅም ሰአት በልሳን መጸለይ አእምሮአችን እንዲሰባሰብና በቀላሉ የጸሎት መንፈስ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል
- በጽናት እየቀጠልን ስንመጣ ቃሎቻችን እያነሱ እና መቃተትና እንደ መንፈስ ፈቃድ የሆነ የጠለቀ ጸሎት መጸለይ እንጀምለን
- መንፈስ ቅዱስ እየመራን የጠለቀ ጸሎት የመጸለይ ደረጃ ላይ ስንደርስ የምንጸልየው ጸሎት ሮሜ 8፡26-27 ላይ እንደሚናገር እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ያለ ጸሎት ስለሚሆን ጸሎቱ የእግዚአብሄርን ልብ ያዘነብላል----------›ድንቅ ነገሮችንም እናይበታለን
እግዚአብሄር ሆይ የጸሎትን ጸጋ አፍስስልን፤የጸሎትንም ሚስጥር ግለጽልን!
No comments:
Post a Comment