Tuesday, September 17, 2013

የምንዘራውን እናጭዳለን




                                                            የምንዘራውን እናጭዳለን
 


መዝራት እና ማጨድ የማያቋርጡ የተፈጥሮ ሂደቶች ናቸው፡፡ሳንዘራና ዋጋ ሳንከፍል በፍጹም አናጭድም፡፡እነዚህ ሂደቶች በመንፈሳዊ ሕይወታችንም በሚገባ የሚታዩ ናቸው፡፡ለምሳሌ ፍቅርን ሳንዘራ ፍቅርን አናጭድም፤ቃሉ አስረግጦ እንዲህ ይላልና፡-“በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ ……….አያቋርጡም” (ዘፍጥረት 8፡22)

እግዚአብሔር በቸርነቱ ሊስበን የሚያደርግልን መልካም የሆኑ ነገሮችና እና ተዓምሮች አሉ፡፡እነዚህ ሁኔታዎች ግን በቀጣይነት ሳያቋርጥ የሚቀጥሉ አይደሉም፡፡በክርስትና ሕይወታችን ማጨድ ከፈለግን ያለ መታከት መዝራት አለብን፡፡ለምሳሌ ቃሉን መስበክ፣መጸለይ፣ለሰዎች በጎ ማድረግ፣ማስታረቅ ወዘተ የምንዘራቸው ነገሮች ናቸው፡፡እነዚህ ዘሮች ደግሞ እንደ ወገኑ በጊዜው ፍሬን ያበቅላሉ፡፡

በሕይወታችን የእግዚአብሔር ቃል እንዲሠራና ፍጻሜያችን እንዲያምር ከፈለገንየእግዚአብሔርን ቃል በልባችን ላይ ያለማቋረጥ መዝራት አለብን፡፡የተዘራው ቃል ተመችቶት እንዲበቅል ደግሞ በቅድስና መኖር፣መጸለይ፣ቃሉን ማሰላሰል እና ቃሉን በተግባር ማዋል ይኖርብናል፡፡
በልባችን ውስጥ ስለሚዘራው የቃል ሂደት እዚህ ጋ መጥቀሱ ተገቢ ነውና፣የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡-

በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግስት እንደዚህ ናትሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል፡፡ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛለው ፍጹም ሰብል ታፈራለች፡፡ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሷልና ወዲያው ማጭድ ይልካል (ማርቆስ 426-28) 

ምድር ምሳሌያዊ(symbolic)ቋንቋ ሲሆን ልብን ይወክላል፡፡ልብ ላይ የሚዘራው ዘርም አራት ሂደቶች እንዳሉት ከቃሉ እንረዳለን፡፡

ዘሩ(የእግዚአብሔር ቃል)---------›ዛላ------------›ፍጹም ሰብል----------›የማጨጃ ጊዜ(በዚህ የቃል መርሕ ጊዜ ወሳኝ እንደሆነ እናያለን)

የእግዚአብሔር ቃል መንፈስ ስለሆነ ውስጣችን ገብቶና ተመችቶት ሲያድግ ብዙ አስደናቂ ፍሬዎችን ያፈራል፡፡አንድ አትክልት ፍጹም ሰብል ላይ ሲደርስ በውበቱ በቁመቱና በሁለንተናው የሚያምር የደረሰ ተክልን እንደሚያሳይ፣በውስጣችን በሚገባ ያደጉ የመንፈስ ፍሬዎች (ክርስትና ከውስጥ ወደ ውጭ ስለሆነ) ለሚመለከቱን ሁሉ የደመቀ መልእክት እንሆናለን ማለት ነው፡፡ይህ ሂደት ግን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል እና ከቃሉ ጋር የተጣበቀ ሕይወትን ይጠይቃል፡፡ “እርሱም እንዴት እንደሆነ ሳያውቅ” የሚለው አባባል የማብቀል እና የማሳደግ ብቃትና ችሎታ የሉአላዊው የእግዚአብሔር እንጂ የሰው ጣልቃ ገብነት እና ችሎታ እንደሌለበት ያስገነዝበናል፡፡ቃሉ ውስጣችን በተገቢው መጠን ሲያድግ የምናያገኛቸው ፍሬዎችም ገላትያ 522-23 ላይ ተዘርዝረዋል፡፡እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡-‹‹ፍቅር፣ደስታ፣ሰላም፣ትእግስት፣ቸርነት፣በጎነት፣እምነት፣የውሀት፣ራስን መግዛት›› የሚያስደንቁ ፍሬዎች ናቸው፡፡እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች ደግሞ በክርስትና ሕይወታችን ስኬታማ እንድንሆን እና የተጽእኖ ሰዎች እንድንሆን ያደርጉናል፡፡በእኔ ግምት ሌላም ተጨማሪ ነገር የሚያስፈልገን አይመስለኝም እነሱ ራሳቸው ከበቂ በላይ ናቸው፡፡


በመጨረሻም ስለ መዝራት እና ስለ ማጨድ ጠንካራ መልእክት ያለው ቃል ላይ ትንሽ ተናግሬ ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡ክፍሉ እንዲህ ይላል፡- “አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፡፡ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል፡፡ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመስራት አንታክት” (ገላ 67-9) ይህ ቃል በተግባር ደረጃ እየሠራነው ያለነውን ነገር እንድንፈትሽ ያሳየናል፡፡እየሠራነው ያለነውም ነገር ከነዚህ ከሚከተሉት ከሁለት ጎራዎች አይወጣም፡-

በሥጋ ስንዘራ----------------›መበስበስን(ኀፍረትን፣ጸጸትን፣ድካምን፣ስንፍናን ብሎም መንፈሳዊ ሞትን እናጭዳለን)
በመንፈስ ስንዘራ------------›የዘላለም ሕይወት(መንፈሳዊ እድገትን፣ስኬትን፣ደስታን፣ሰላምን ወዘተ

ስለዚህ የምንዘራው ዘር ላይ በሚገባ ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም የምንዘራው ዘር ነው ስኬታችን፣ምልልሳችንን፣ተጽእኖአችንን እና ፍጻሜያችንን የሚወስነው፡፡ሳናስተውል በሥጋ የምንዘራቸው ነገሮች የክርስትና ሩጫችንን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩበት ከምንደርስበት ጉዞ ላይ በብዙ ልንዘገይ ልንዘገይ እንችላለንና፣ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡እግዚአብሔር የመርሕ አምላክ ነውና በሥጋ መጥፎ ነገርን እየዘራን፣ በፍጹም መልካም ነገሮችን አንጠብቅ፤ቃሉ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ያጭዳል” ይላልና!



No comments:

Post a Comment