Wednesday, September 18, 2013

መታከትን የማስወገጃው ምስጢር




መታከትን የማስወገጃው ምስጢር


መታከት የሚለው ቃል መሰላቸት፣ፍላጎት ማጣት ፣ተስፋ መቁረጥ፣ኃይል ማጣት የሚሉትን ሐሳቦች ይወክላል፡፡በክርስትና ሕይወታችን ሊያታክቱን የሚችሉ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ለምሳሌ ለውጥ ማጣት፣የመከራ ብዛት፣ስደት፣ደጋግሞ መውደቅ፣መገፋት ወዘተ በአበይትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ሊያታክቱን የማይመጡ ጫናዎች የሉም፡፡የኢየሱስን ሕይወት በሥጋችን ተሸክመን ስለምንዞር(2 ቆሮ 410) ለብዙ ልብን ለሚያዝሉ ነገሮች እንጋለጣለን፡፡መታከት ደግሞ ክፉ መንፈሳዊ ውጤት አለው፡፡መታከት የሚለውን ቃል ሳሰላስል ወደ ሐሳቤ የመጣውን አሉታዊ ሰንሰለት ላስቀምጥ፡-

  • ወደ ሕይወታችን የሚመጡ ጫናዎች

  • የጸሎት ሕይወትና ከቃሉ ጋር ያለን ሕብረት መቀዝቀዝ

  • ለዲያቢሎስ ጥቃት በቀላሉ መጋለጥ

  • መታከት

  • መሸነፍ------------›መውደቅ


በሕይወታችን ለመታከት የሚያጋልጡን ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡በበቂ ሁኔታ አለመጸለይና ከጌታ ቃል ጋር በቂ ሕብረት አለማድረግ ግን እንደ ዋነኛነት ሊቆጠሩ ይችላሉ፡፡የእግዚአብሔር ቃል ተግባር መፍታት እንቅልፍ ታመጣለች፤የታካችም ነፍስ ትራባለች(ምሳሌ 1915) ብሎ ይናገራል፡፡በእግዚአብሔር ፊት ትጉሕ አለመሆኑ ጠንቁ ብዙ ነው፡፡የእግዚአብሔርን ቃል በበቂ ሁኔታ አለማንበብ፣አለማጥናትና አለማሰላሰል መንፈሳችን ደካማ እንዲሆን ስለሚያደርገው በቀላሉ ልንታክት እንችላለን፡፡ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች መንፈሳቸው ሲጠነክር ማንኛውንም ጫናን መቋቋም እንደሚችሉ በማሰብ፣በውስጡ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ(ኤፌሶን 316) ብሎ እንደ ጸለየላቸው ማሰብ ተገቢ ነው፡፡የውስጡ ሰውነታችን በኃይል የሚጠነክረው ደግሞ ከቃሉ ጋር በምናደርገው ሕብረትና የጠለቀ ጸሎት ነው፡፡አለበለዚያ ግን ተቃራኒው ይሆናል-መሰላቸትና መታከት!


ሌላው ምክንያት ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ድምጽ ይልቅ የሥጋንና የነፍስን ድምጽ ስንከተል፣እምነታችንና ጽናታችን ስለሚሸረሸር በቀላሉ ልንታክትና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፡፡ስለዚህ ስሜቶቻችን፣ነፍሳችንና ስጋችን የሚለንን ሳይሆን መንፈስ የሆነው ቃል የሚለንን ለመሆንና ለመተግበር መጨከን ምንም አማራጭ የለውም፡፡ይህ ደግሞ መታዘዝን ይፈልጋል፡፡


በብዙዎች ዘንድ ራእይ ወይም መገለጥ ሲጠፋ መታከት ሊመጣ ይችላል፡፡ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃልለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ሚስጥር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው (ሮሜ 1626) በማለት የሚናገረው፡፡አዎ! የወንጌል እውነት በበራልንና በተገለጠልን መጠን ነው እየበረታን የምንመጣው፡፡ በተገላቢጦሽ መንፈሳዊ ራእይ፣መገለጥና መረዳት ከሕይወታችን ሲጠፋ ሕይወታችን በድግግሞሽ ይዋጥና ልንታክት እንችላለን፡፡


ሌላው ትልቅ ምክንያት የአጋንንት ተጽእኖ ነው፡፡የእግዚአብሔር ቃል ባላጋራችን ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል (1 ጴጥርስ 58)ብሎ ያስጠነቅቃል፡፡አንዱና ዋነኛው መንገድ ሊውጠን የሚጠቀምበት መንገድ ደግሞ መታከትን ወደ ሕይወታችን በማስረጽ ነው፡፡አትችልም፣አይሳካልህም፣የት አለ ፍሬህ፣ተሰሚነት የለህም ፣አርፈህ ብትቀመጥ ይሻላል ወዘተ እያለ አእምሮአችንን በመደብደብ የጀመርነውን ሥራ ሊያስጥለን ይተጋል፡፡ስለዚህ ንቁ በመሆን በኃይል መቃወም አለብን፤በቃሉ ሰይፍም መዋጋት ይኖርብናል፡፡


እንደ አዲስ ኪዳን አማኝ እንዳንታክት እግዚአብሔር በክርስቶስ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል(2ጴጥ 12-3)፡፡ስለዚህ በቃሉ ላይ ቆመን አንታክትም እንላለን፡፡በትጋት ከገሠግሥን ላንታክት የምንችልባቸው ምክንያቶችም እንደሚከተሉት ተጠቅሰዋል፡-


1.በውስጣችን ከክብር ወደ ክብር እንድንለወጥ የሚያደርግ መንፈስ ስላለ አንታክትም፡- 2ቆሮንቶስ 3 የምእራፉ መጨረሻ ላይ መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን(ቁ.18፤አጽንኦት የእኔ) ይላል፡፡ እንደሚደረግ የሚለውን ልብ በሉልኝ፡፡ይህ ማለት በውስጣችን መታከት እንዳይመጣ ይልቁንም መንፈሳዊ ለውጥና እድገት እንዲኖረን የሚሠራና የሚያተጋን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አለ ማለቱ ነው፡፡ከዚህ የተነሳ የሚቀጥለው ምእራፍ መጀመሪያ ላይ ስለዚህ አንታክትም (2 ቆሮንቶስ 4፡1) ይላል፡፡ይህ አባባል ከምእራፍ ሦስት ጋር ተያያዥነት እንዳለው ልብ ይሏል፡፡

2.ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ እቃ ውስጥ ስላለን አንታክትም
በውስጣችን ያለው መዝገብ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ጎማ ተወጥሮ እንዲቆይ በከመነዳሬ ውስጥ ያለው አየር እንደሚጠቅም ሁሉ በውስጣችን ያለው መዝገብ(ባከማቸነው ልክ)ከመታከትና ተስፋ ከመቁረጥ ይጠብቀናል፡፡የዚህን የመዝገብ በውስጣችን የመኖር ጥቅም ሲገልጽ  እንዲህ ይላል፡- በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤እናመነታለን እንጂ ተሰፋ አንቆርጥም፤እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም (2ቆሮንቶስ 48) ፡፡ትልቁ ነገር በውስጣችን ያለውን እምቅ ሀብት መንገዘቡ ነው የኛ ኃላፊነት፤ቃሉበጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ (ምሳሌ 156) ይላልና!


3.አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን(2ቆሮንቶስ 413) አንታክትም፡--ቃሉ በግልጽ እንደሚናገር እምነት ጽናትን ያመጣልና(ኢሳይያስ79)!


4.የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ስለሚታደስ (2ቆሮ 416)አንታክትም

ይህ የመጨረሻው ምንባብ በተለይ በክርስትና ሕይወታችን ዋና ቁልፍ ነገር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ሐሳቡ መታከት እና መሰላቸት ወደ ሕይወታችን እንዳይመጣ የማያቋርጥ ጸሎትና ከቃሉ ሕብረት እንደሚያስፈልገን ነው የሚያሳየን፡፡ልክ ባትሪ ሲደክም በአሌክትሪክ ቻርጅ እንደሚደረግና እንደገና ሊሠራ እንደሚችል ሁሉ ስንጸልይ(በተለይ በመንፈስ ስንጸልይ) እንታነጻለን፤ኃይላችን ይጨምራል፤ተስፋችን ይታደሳል ብሎም እንደገና ለቀጣይ ሥራዎች እንጠናከራለን፡፡ይህ ዲሲፕሊን የሚያስፈልገውና በቀጣይነት ያለማቋረጥ መተግበር ያለበት የሕይወት ዘመን ኃላፊነታችን ነው፡፡ለዚህ ነውዕለት ዕለት ይታደሳል”  ብሎ የሚናገረው-የዕለት ተዕለት ተግባር!


ቢሆንም መታከት ወደ ሕይወታችን ሊመጣ የሚችል እውነታ ነው፡፡ይህንን ሃቅ በመግቢያም ላይ ጠቅሻለሁ፡፡በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ምን እናድርግ ለሚለው ስድስት ተግባራዊ ርምጃዎችን በመጥቀስ ጽሑፌን ልጨርስ፡-
1.ጠንከር ያለ የጸሎትና የጽሞና ጊዜዎችን እንያዝ(ከጾም ጋር ቢሆን የበለጠ ይመረጣል)
2. መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ እናንብ፣ቃሉን እናጥና እንሰላስለው፡፡በተጨማሪም ካለንበት ሁኔታ ጋር የሚሄዱ አነቃቂ መንፈሳዊ ጽሑፎችን እናንብ
3.ከእኛ በሚሻል የክርስትና ሕይወት ላይ ካሉ ባልደረቦች ጋር በመገናኘት እንመካከር እንጸልይ
4.የአጋንንትን ምሽግ ለማፍረስ በእምነትና በመንፈስ እየተቃወምን እንጸልይ
5.የጠላት ተጽእኖና ደባ ሊኖር ስለሚችል እራሳችንን ትሑት በማድረግ ይጸለይልን
6.ባለንበት ሁኔታ ላይ ሊረዱን የሚችሉ ጤናማ ስብከቶችንና ትምሕርቶችን እንስማ


የኃይል ምንጫችን እግዚአብሔር በመሆኑ ፊቱን በመሻትና በእግሩ ስር በመሆን ስንጠባበቀውና ስንፈልገው ታማኝ ነውና ይመጣል፤ያድሰናልም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው አይደክምም አይታክትም ማስተዋሉም አይመረመርም፡፡ለደካማ ኃይልን ይሰጣል ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል፡፡ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል ጎበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ (ኢሳ 4031)  የሚል ግሩምና ድንቅ የተስፋ ቃል አለን፡፡አዎ! ደጋግሞ መታወቅ ያለበት ነገር ሁላችንም ልንታክት፣ልንሰለች፣ተስፋ ልንቆርጥና ልንወድቅ እንችላለን::ነገር ግን በዚህ ጊዜ ወደ ጌታ ዘወር ብለንና ወስነን በትግእስትና በጸጥታ በጸጋው ዙፋን ፈት በቂ ጊዜን ብንወስድእግዚአብሔር የምሕረት አምላክ ነውና ያድሰናልያበረታናል እንደገናም በክንፍ እንድንወጣ ያደርገናል፡፡

ጉልበትን የሚያድስና የሚያበረታ አምላክ ከዘላለም እስከዘላለም የተባረከ ይሁን!



                                                                                                                                           



                                                                                                                                                                                   


                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                            

No comments:

Post a Comment