Saturday, September 7, 2013

መለኮታዊ ገጠመኝ(holy encounter with God)


                          


ድንቅ መለኮታዊ ገጠመኝ(holy encounter with God)

ባለፉት ዘመናት በጽሁፍ ላይ ያየናቸው መለኮታዊ የሆኑ ጉብኝቶችና ገጠመኞች አሁንም በዚህ ዘመን በሚገባ ሲከሰቱ ይስተዋላል፤መለኮታዊ ጉብኝት ጊዜ ያለፈበት ጉዳይ አይደለም፡፡
ከጌታ ጋር አብዛኛውን ጊዜ የምንገናኘው ቃሉን ስናነብና ስጸልይም ቢሆንም አንዳንዴ እኛ ባለሰበነው መንገድ እራሱን ገልጦልን ህይወታችን እስከወዲያኛው ሊቀየር ይችላል፡፡እንደዚህ አይነት ክስተት ያልጠበቅነውና በእራሱ ጊዜ ራሱ ባቀደው ሰአት ስለሚሆን በፍጹም በህይወታችን ልንረሳው አንችልም፡፡እንዳልኩት ይህን መለኮታዊ ገጠመኝ እኛ ልናቅደውና በፈቃዳችን ልንለማመደው አንችልም፡፡ከእኛ የሚጠበቀው መንፈሳዊ ጆሮአችንንና አይኖቻችንን ከፍተን ለመቀበል ንቁ መሆን ነው፡፡
መለኮታዊ ገጠመኞች ወደ ህይወታችን እንዳይመጡ ምን ከለከለን ?
  • ልባችን በብዙ ነገር ተይዟል
  • ጆሮአችን በሌሎች በማይረቡ ነገሮች ተደፍኗል
  • ጠበቅ አድርገን የጌታን ፊት መፈለግ አቃተን
መለኮታዊ ገጠመኝ ወይም ጉብኝት(holy encounter) ሲመጣ ምንድነው የሚሆነው ?
  • አንድ የእግዚአብሄር ሰው እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹an encounter with God opens our eyes to recognize His unapproachable superiority››
  • ህልውናው በሚገርም ሁኔታ ይታወቀናል
  • ያለሱ የማንረባ ሰዎች መሆናችን እናውቃለን
  • የእግዚአብሄርን መሀሪነት እንገነዘባለን
  • በተግባር ደረጃ ታዛዦች እንሆናለን፡-ምን እንዳደርግ ትወዳለህ እንለዋለን
በኢዮብ መጽሀፍ ላይ ኢዮብ ወደ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው መንፈሳዊ አቋም በሚቀጥለው ጥቅስ ተንጸባርቋል፡፡እንዲህ የሚል ነው፡-‹‹ጽድቄን እይዛለሁ እርሱንም አልተውም ከቀኖቼ ሁሉ ስለ አንዱ ልቤ አይዘልፈኝም››፡፡ከጓደኞቹ ጋር በርከት ያለ ምእራፎች ሲከራከር ከቆየ በኋላ እግዚአብሄር ክብሩንና ማንነቱን በሚገባው መንገድ ሲገልጽለት ከመጀመሪያው አቋሙ እጅግ የሚለይና የልብ መሰበር የታየበት ምላሽ ነበር የነበረው፡፡እንዲህ በማለት ፡-‹‹መስማትን በጆሮዬ በመስማት ሰምቼ ነበር አሁን ግን አይኔ አየችህ ስለዚህ እራሴን እንቃለሁ፤በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ›› እጅግ የሚገርም እና ለጌታ የተንበረከከ ሰው ቋንቋ!ለዚህ ምላሽና መንበርከክ ያበቃው የእግዚአብሄርን ታላቅነትና ሁሉን ቻይነቱን በመንፈሱ ማየቱ ነው፡፡
እግዚአብሄርን በግርማውና በክብሩ ማየት አስደንጋጭና አስፈሪ ልምምድ ቢሆንም በሕይወታችን የማንረሳውና በውስጣችን ታትሞ የሚቀር ስለሚሆን ለመንፈሳዊ እርምጃችን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡አንድ የእግዚአብሄር ሰው በጻፉት መጽሃፋቸው ላይ የእግዚአብሄር ሰዎች ጌታን ለማገልገል ሲነሱ እንዲህ አይነት ገጠመኝ (traumatic experience) ቢኖራቸው መልካም ነው ይላሉ፡፡
እንዲህ አይነት ገጠመኝ ወይም ጉብኝት(holy encounter) በህይወታችን ትልልቅ ለውጦችን ያመጣል ፡፡ለምሳሌ፡-
  • የልብ መሰበር
  • ጥልቅ ንስሀ
  • በቃላት መናገር የማይቻል ደስታና መረጋጋት
  • ታዛዥነት
ኢሳ 6፤1-8 ላይ የተከሰተው ነገር በኢዮብ ላይ ከተከሰተው ሁኔታ ጋር ቢለያይም የሚያመሳስላቸው ነገር ግን ላዩት ነገር የሰጡት ምላሽ ነው፡፡በሁለቱም ህይወት የልብ መሰበር ታይቷል፡፡ነቢዩ ኢሳያስ እግዚአብሄርን በሚገርም ግርማና አስፈሪ ክብር ሲያይ እንዲህ አለ፡-‹‹ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ህዝብ መካከል በመቀመጤ አይኖቼ ጌታ ንጉሱን እግዚአብሄርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ ››ልቡ የተሰበረ ሰው ቋንቋ!
በእኛም ህይወት እንዲህ ነው የሚሆነው፡፡የጌታን ግርማ፣ሀያልነት፣ቅድስናና ክብሩን እስክናይ ድረስ ሰዎችን አብጠልጣይ፣ትእቢተኛ፣ኩሩ፣አትንኩኝ ባይ፣ተናጋሪ፣ከሳሽና ግትር ነን፡፡እርሱን በክብሩ ስናየው ግን ነገሮች 360 ዲግሪ ይቀየራሉ፡፡በሚገርም ሁኔታ እንቀየራለን እንለወጣለን!
ከላይ የተገለጸው አይነት መለኮታዊ ገጠመኝ ወይም ጉብኝት(holy encounter) ሲያገኘን በማይረሳ ሁኔታ ህይወታችን ስለሚለወጥ እንደ እዮብ ‹‹እራሴን እንቃለሁ›› ወይም እንደ ነቢዩ ኢሳያስ ‹‹ጠፍቻለሁ ወዮልኝ›› እንላለን እንጂ ሌላ ቋንቋ አይኖረንም፡፡ስለዚህ ይህንን መሰል ቅዱስ ገጠመኝ ወይም ጉብኝት (holy encounter) እንዲያገኝን በጌታ ፊት እንውደቅ!





No comments:

Post a Comment