Wednesday, September 11, 2013

ቃሉን የማሰላሰል ጥቅም

                                                   ቃሉን የማሰላሰል ጥቅም


ቃሉን ማሰላሰል ሕይወታችንን እንደሚለውጥ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ችግሩ ባልተከፋፈለ ልብ በትጋት እና በጥሩ ዲሲፕሊን መተግበሩ ላይ ነው፡፡እንደምናየው ብዙ ሰዎች ስለ እራሳቸውም ሆነ ስለሚሠሩት ስራ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው የሚያስቡት፡፡ቆም ብለው ቃሉን በማሰላሰልና ከሕይወታቸው ጋር በማዛመድ እራሳቸውን አያዩም ድርጊቶቻቸውን አይመረምሩም፤መሮጥ ብቻ እንጂ!


የእግዚአብሔር ቃል “ባላጋራችን ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችን ይዞራል” (1 ጴጥሮስ 5፡8)ይለናል፡፡አዎ! ግሩም ምክር ነው፡፡ካልተጠነቀቅንንና ካልነቃን ሰይጣን አእምሮአችንን በመከፋፈልና ለጌታ እንዳንሰጥ በማድረግ የቃሉ በረከት ወደ ሕይወታችን እንዳይመጣ በማድረግ ፍሬ ቢስ ሊያደርገን ይችላል፡፡ከዚህ ሁሉ ችግር የሚያወጣን ለቃሉ ያልተከፋፈለ ልብን መስጠት ነው፡፡


መዝሙር 1፡1-3  ለስኬታችህ ቁልፍ መርሖዎችን የያዘ ክፍል ሲሆን፣ቃሉን የማሰላሰልን ጥቅም በሚገባ ያሳየናል፡፡ክፍሉ እንዲህ ይላል፡-


“ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ ፤በኃጢአተኞች መንገድ ያልቆመ፤በዋዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ፡፡ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፤ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል‹‹he meditates››፡፡እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፤ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤የሚሠራውም ይከናወንለታል”


ይህ ቃል የእግዚአብሔርን ቃል ማሰብና ማሰላሰል ያሉትን ሦስት ጥቅሞች ያሳየናል፡-


•    በክርስትና ሕይወት በሚገባ መተከልና መደላደል
•    የማያቋርጥ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት
•    መለኮታዊ ስኬት

ቃሉን ማሰላሰል በሕይወታችን የጸሎት መንፈስ(the Spirit of prayer) እንዲኖር ያደርጋል፡፡ባነበብንና ባሰላሰልን ቁጥር ለጸሎት እንገፋፋለን፡፡እንዳውም የማያቋርጥ አዎንታዊ ሂደት(positive vicious cycle) በሕይወታችን ይመጣል፡፡ይህንን ሂደት እንዲህ ገልጨዋለሁ፡-


ቃሉን ማንበብ እና ማሰላሰል--------›የጸሎት መንፈስ-------›በጨመረ ሁኔታ ቃሉን ማንበብና ማሰላሰል----------›የጸሎት መንፈስ መጨመር -------›የጸሎት መንፈስ መጨመር --------›ይቀጥላል



ከአራቱ እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ የክርስትና ዲሲፕሊኖች (ጸሎት፣ጾም፣ቃሉን ማጥናት ማሰላሰልና ቃሉን በተግባር ማዋል) አንዱ ቃሉን ማሰላሰል ነው፡፡አብዛኛውን ጊዜ ጸሎትና ቃሉን ማሰላሰል አብረው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው፡፡በእንደዚህ አይነት ዲሲፕሊን ስናሳልፍና ስንተጋ መንፈሳዊው ዓለም እየተገለጠልንና እየበረታን እንመጣለን፡፡አንድ በእንግሊዝኛ ያገኘሁት መርሕ አለ፡-
Meditation(ማሰላሰል)-------›Revelation(መረዳትና መገለጥ)---------› application(ቃሉን መተግበር)

ይህንን መርሕ ሳሰላለስል የገባኝ ነገር ያልተገለጠልንን፣ያልተረዳነውንና ያላስተዋልነውን ቃል በተግባር ማዋል እንደማንችልና ዳገት እንደሚሆንብንና በተቃራነው ደግሞ በውስጣችን በማሰላሰል የተዋሃደውን ቃል በተግባር ማዋል እንደማያዳግተን ነው፡፡እዚህ ጋ የምንከፍለው ዋጋ ነው፣የሚታይ ክርስትናን እንድንኖር የሚያደርገም፤መጨከን የሚያስፈልገው!
ንጉሥ ዳዊት “አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” (መዝ 119፡11) ብሎ ተናግሯል፡፡ትልቅ መርሕ! በልባችን ውስጥ ቃሉን የምንሰውርበት አንድ ጥሩ መንገድ ቃሉን ማሰላሰል ነው፡፡በልባችን የተሰወረውና የጠበቅነው ቃል በፈተና ጊዜ ይጠብቀናል፤ከክፉ ነገሮች ያወጣናል፡፡እንዳውም የእግዚአብሔርን መንፈስ ከማሳዘን ያድነናል፡፡ይህ ነው ትልቁ ትርፋችን!


በተጨማሪም ቃሉን ማሰላሰል የቃሉ ኃይል በሕይወታችን እንዲለቀቅ ያደርጋል፡፡ከቃሉ ጋር ሕብረታችን በጨመረ ቁጥር፣የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን ይጨምራል፡፡ከዚህም የተነሣ ያለን ተጽእኖ እየሰፋና ለብዙዎች በረከት እንሆናለን፡፡ስለዚህ ለቃሉ ያልተከፋፈለ ልብን እንስጥ! ጌታ ሆይ እርዳን!





No comments:

Post a Comment