እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች ይናገራል
እግዚአብሔር በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ሊናገረን እንደሚችል መዝ 19፡1-14 አዘውትሮ የሚጠቀስ ክፍል ነው፡፡በዚህ ከፍል ባለው ምንባብ መሠረት
እግዚአብሔር ፡-
1.በሚታየው ዓለም ባሉ
ግዙፍና ድንቅ የእጁ ሥራዎቹ ይናገረናል
ይህንን ሐሳብ በሚገባ የሚገልጽልን ቃል የሚከተለው
ክፍል ነው፡- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤የሰማይምም ጠፈር የእጁን ስራ
ያወራል፡፡ቀን
ለቀን ነገርን ታወጣለች፤ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች፡፡ነገር የለም መናገርም የለም ድምጻቸው አይሰማም፡፡ድምጻቸውም ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ አለም ዳርቻ ወጣ” (መዝ 19፡1-4)
ሰማያት ቃል የላቸውም፡፡ቢሆንም በሚገባን ሁኔታ እነሱን የከሸነና የፈጠረ ኃያል አምላክ እንዳለ ይናገራሉ፡፡አልበርት አንስታይን “the more I study
science,the more I believe God”/ብዙ ሳይንስን ባጠናሁ ቁጥር ፣እግዚአብሔርን የበለጠ እንዳምን ሆኛለሁ” ብሎ ተናግሯል፡፡አዎ!ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ሁኔታ እንዲናገሩ ሆነው ተፈጥረዋልና፣ትክክል ብሏል፡፡
2.መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠን ስናነብ ይናገረናል
ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በትሕትና ቀርበን በሰከነ ሁኔታ ብናነበውና ብናጠናው ያስደንቀናል፡፡የእግዚአብሔር ቃል “በእውቀት
ከከበረውና
ካማረው ሀብት ጓዳዎች ይሞላሉ” (ምሳሌ 24፡4) እንደሚል ጊዜ ሰጥተን መጽሐፍ ቅዱሳችንን ብናጠና በእውቀት እንሞላለን፤ጌታ ውስጡ በታጨቁት ወርቃማ ቃሎቹ ይናገረናል፤አካሄዳችን በማስተካከል ፍጻሜያችንን ይቀይራል፡፡ከእኛ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው-እንዲናገረን ፈቃደኝነት፡፡ልባቸንን ከከፈትንና ፈቃደኛ ከሆንን በሚገባ ይናገረናል፡፡የእግዚአብሔር ቃል ሲናገረን ደግሞ ውጤት አለው፤ብዙ ፍሬን ያፈራል፡፡መዝ 19፡7-11(ያንቡት) የእግዚአብሔር ቃል ሲናገረንና ወደ ውስጣችን ሲገባ ያሉትን ለውጦች በሚደንቅ ሁኔታ ዘርዝሯቸዋል፡፡የእግዚአብሔር ቃል ነፍስን ይመልሳል(ነፍስን ከጥፋት ያስመልጣል)፣ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል(ብስለት ከፈለጋችሁ ወደ ዚህ ቃል መምጣት ነው፤ከምትገምቱት በላይ ይቀይራችኋል)፣ዓይንን ያበራል(መንፈሳዊው ዓለም እንድንረዳው ያደርጋል)፣ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል(በምድራዊ ቋንቋ መግለጽ የማይቻል ሐሤትና ደስታ አለው)::እናም የሰማነውን
ቃል ስንጠብቀው፣በሁሉም የሕይወታችን አቅጣጫ ይጠቅመናል፡፡
3.በመንፈሱ ለልባችን ይናገረናል
እዚሁ በመዝሙር 19 ፡12-14(ያንቡት) ባለው ክፍል፣ዳዊት በጸሎት ቋንቋ የሚገርም መንፈሳዊ ሚስጥርን ይናገራል፤እንዲህ በማለት፡-“ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ፡፡የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ፡፡አቤቱ ረድኤቴ መድኃኒቴም የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” እዚህ ቃል ላይ እየተናገረ ያለው መንፈስ ቅዱስ ውስጣችንን እየፈተሸና እየመረመረ በብርሃኑ ካልስታወቀን በስተቀር፣ከእኛ የተሰወሩ ጸያፍ ነገሮች በውስጣችን እንደሚኖሩ ነው፡፡በዝርዘር መጥቀስ ካስፈለገ የተጠቀሱ ሦስት አንኳር ኃጢአቶች ናቸው፤በውስጣቸው ብዙ ዝርዝር ነገር ቢኖራቸውም፡፡እነሱም፡-
- የተሰወረ ኃጢአት
- የድፍረት ኃጢአት
- ግብዝነትና ሽንገላ(የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን የሚለው ይህንን ያሳየናል)
የእግዚአብሔር መንፈስ ረድቶን ካላሳየንና ካልተናገረን፣ንጹህ የሆንን መስሎ ተኩራርተን ልንቀጥል
እንችላለን
የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡ነገር
ግን በጌታ ፊት ከምር ወድቀን እባክህ በልባችን ተሰውረው ያሉ አንተ የማትወዳቸውን እርሞችን አሳየን ብለን በቅንነት ብንጮህ፣በሚገባን መንገድ ይናገረናል ያሳየናልም፡፡እነዚያን እርም የሆኑ ነገሮች ያኔ በመታዘዝ አንቅረን ብንተፋቸው ግንኙነታችንን እና ሕብረታችን እየጠለቀ ይመጣልና፣ለውጡ ቀላል አይሆንም፡፡በቀጣይነትም ከሱ ጋር ያለንን ግንኙነት በጸሎት ብናጠብቅ፣ቃሉን ብናሰላስልና ብናጠና እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወታችን ስለሚመጣ የድፍረት ኃጢአቶችን የመተው አቅም እናገኛለን፡፡ከዚህም የተነሣ መንፈሳችን ንቁ (sensitive) ስለሚሆን እርሱን በየትኛው መልኩ መበደል እየከበደንና እየተቀደስን እንመጣለን፡፡እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚናገረንም በሦስት ሁኔታዎች ነው፡፡እነሱም፡-
- በሕሊናችን (thru our conscience)
-------›የእግዚአብሔር መንፈስ ቀድመን ያነበብናቸውን ቃሎች ወደ ሕሊናችን በማምጣት ድርጊቶቻችን እንድናመሳክር በማድረግ ይናገረናል፤እንድናስተካክልና በራሱ መንገድም እንድንራመድ ያደርገናል
- በለሆሳስ ድምጽ(subtle small voice)
--------›የእግዚአብሔር መንፈስ በተለያዩ የሕይወት ሁኔታዎች ስናልፍ አቅጣጫ ሊሰጠን፣ሊያጽናናን፣ሊያቀናን ወዘተ ኩልል ባለች ልብን በምታሳርፍ ድምፁ ለልባችን ይናገረናል
- ጮክ ባለ ድምጽ (authoritative voice of the Holy Spirit)
---------›መስመራችን ተንጋዶ፣አልሰማ ብለነው፣እየሄድንበት ያለው መንገድ አደጋ ከሆነና ወይም መንታ በሆነ መንገድ ላይ ሆነን ስንቸገር አንዳንዴ ጮክ ባለ ድምጽ ሊናገረን ይችላል፡፡ይሄኛው ሁልጊዜ የሚሆን ክስተት አይደለም፡፡
የእግዚአብሔር ቃል “በአንድም በሌላም ይናገራል ሰው
ግን አያስተውልም”(ኢዮብ 33፡14 ) ይላል፡፡ይህ ቃል እውነት ነው፡፡የሰው ፍጥረት በእንቅልፍ ውስጥ ስላለ ነው እንጂ እግዚአብሔር ያልተናገረበት ዘመን የለም፡፡በዚህ ዘመን ደግሞ ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በኢየሱስ በኩል ያለ ማቋረጥ እየተናገረን ነው ያለው፡፡ስለዚህ እባክህ ጌታ ሆይ ጆሮዬን ክፈተው፣ዓይኔን ግለጠው፣መንፈሴን አንቃውና ተናገረኝ እንበለው፡፡እርግጠኛ ነን ልባችን ከተዘጋጀና በሰከነ ሁኔታ በእግሩ ስር ከተቀመጥን በሚገባን መንገድ ይናገረናል፡፡
እባክህ ጌታ ሆይ ለእያንዳንዳችን በሚገባን መንገድ ለልባችን ተናገረን!
No comments:
Post a Comment