Friday, March 27, 2015

ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ



ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ

ይህንን አጭር ጽሑፍ ከማዘጋጀቴ ከሦስት ቀን በፊት የሦስት ሰዎችን ሞት በተከታታይ ሰማሁ፡፡ከእነዚህም አንዱ የምወደው አባቴ ነበር፡፡ለ 8 ዓመታት ያህል በአካል ከተለያየን በኋላ፣አንዴ እንኳ ደግሜ ላየው የምችልበት ዕድል አጥቼ ላንገናኝ እስከ ወዲያኛው ተለያየን---ያሳዝናል! ታዲያ ሞት አይቀርምና፣ሌላው ተረኛ ተራውን ይጠብቃል፡፡እስከዚያም ሕይወት ትቀጥላለች!

ሁል ጊዜ ከፍጥረታችን የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ሌላ ሰው ሲሞት ሸምግሎ ነው፤ታሞ ነበር፤ራሱን አይጠብቅም ነበር ወዘተ የሚሉ ምክንያቶችን ለአእምሮአችን በመስጠት፣የሟቾችን አሟሟት አግባብ ነው ብለን ልባችንን እናሳርፋለን፡፡ነገር ግን የኛን ሟችነት በመካድ፣ባለማመንና ባለመቀበል ነው ዘመናችን የሚነጉደው፡፡ሆኖም መታወቅ ያለበት ነገር ሟችነታችን 100 % አይቀሬ መሆኑን ነው፡፡

ሌላው የሚገርመኝ ነገር፣የክርስትያኖችን የሕይወት ምልልስ ስቃኝ፣የሚታየውና የሚሰማው ነገር ሁሉ አሳዛኝ እየሆነ ነው ያለው፡፡ብዙው ክርስትያን ሟችነቱን የዘነጋው ስለሚመስል፣ከምድራዊ ነገር ተጣብቆ ይስተዋላል፡፡እንደ ሐጌ ዘመን ሰዎች፣በዚህ ዘመን ልቡን በመንገዱ ላይ ያደረገና የጨከነ ሰው እምብዛም አይታይም(ሐጌ 1፡5፣7)፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስትያን ልቡን በመንገዱ ላይ ማድረግ እንዳለበት ሲመክር እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።ሞታችኋልና፣ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና።ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፣በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ……….” (ቈላ 1፡1-5) ብሎ ተናግሯል፡፡

የሚገርምና የሚደንቅ ምክር ነው፡፡እዚህ ምንባብ ውስጥ እንዳያችሁት ከምድር ስበት የሚያላቅቁን ሁለት ነጥቦች ተጠቅሰዋል፡፡የመጀመሪያው “በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም” የሚለው የመፍትሔ ሐሳብ ነው፡፡እዚህ ጋ ነው ትልቅ የውሳኔ ርምጃ መውሰድ የሚኖርብን፡፡የጨለማው ገዢና ይህች ዓለም ምድራዊና ሥጋዊ የሚያደርጉን በሌላ አይደለም፣የምናስበውን በመሻማት እንጂ፡፡የምናስበውና ጊዜአችንን የምንሰጥለት ነገር ደግሞ ሩጫችንንና ፍጻሜአችንን በእጅጉ ይወስነዋል፡፡ለመሆኑ አእምሮአችንን የያዘውና አዘውትረን የምናስበው ምንድነው? እንግዲያው እሱው ራሱ ነው የሚወርሰን፡፡

ሁለተኛው “በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ” የሚለው ምክር ነው፡፡ይህ ሐሳብ ከመጀመሪያው ጋር የተያያዘ ነው፡፡የምናስበውን ስንመርጥ ብልቶቻችንን እየገደልን እንደ ሆነም ሊታወቅ ይገባዋል፡፡በተጨማሪም በጾም፣በጸሎትና ከቃሉ ጋር በሚኖረን ቁርኘት የሥጋ ሥራዎችን እንገድላለን፤ክርስትና ዕለት ተዕለት እየተሞተ የምንኖረው ኑሮ ነውና፡፡ኧረ ለመሆኑ ልቡን በመንገዱ ላይ ያደረገ ሰው ሌላ ምን ሥራ ይኖረዋል? የአመጻ የጦር ዕቃ እንዳይሆኑ በምድር ያሉቱን ብልቶቹን መግደል እንጂ፡፡በቃ እነዚህ ሁለቱ ናቸው የሕይወት ዘመን የክርስትያን ሥራዎች-ማሰብና መግደል! ሌላው ነገር ሁሉ ከነዚህ ሁሉ ተግባራት እንደ ፍሬ ይመነጫል፡፡

አዎ! ወገኖቼ ልባችንን በመንገዳችን ላይ እናድርግ፡፡የዚህ ምድር ኑሮ እጅግ ጊዜያዊና ኀላፊ ነው፡፡የሚበልጥ ርስት እንዳለን እያሰብን ሊተበትበንና ከምድር ጋር ሊያጣበቀን ከሚፈልግ ማንኛውም አካሄድ ራሳችንን እንጠብቅ እንንቃ!

ጌታ ይርዳን!

No comments:

Post a Comment