Wednesday, August 21, 2013

ለጌታ ሊኖረን የሚገባ በቂ ምላሽ



ለጌታ ሊኖረን የሚገባ በቂ ምላሽ

መሀልይ 51-6
በዚህ ምእራፍ ውስጥ ያለችው ተዋናይ ሴት ስለውዷ በቂ እውቀት የነበራት ሴት ስትሆን ሊጎበኛት ሲመጣ
  • በቂ ምላሽ ለመስጠት ዘገየች
  • አጥጋቢ ምላሽን ባለመስጠቷ ውዷ ጥሏት ሄደ
  • ከዚህም የተነሳ የደረሰባትን መከራ እናያለን
ለዚች ባለእድል ሴት የቀረበው ግብዣን መሀ 51 ላይ እናገኘዋለን፡፡እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹እስክትረኪ ድረስ ጠጪ››
ከዚህ አውደ ንባብ የምንረዳው አንድ ነገር አለ፡፡ውዷ ወደ ዚች ሴት የመጣበት ምክንያት ጠጥታ እንድትረካ ነው፡፡በእኛም ህይወት የጌታ ከፍ ያለው ሃሳብ ከእርሱ ጋር ከሚኖረን ህብረት የተነሳ ስለምናገኘው ህብረት እና እርካታ ነው፡፡ይህም እረፍትና እርካታ በህይወታችን ሲኖር ጠንካራና የሚታይ ምስክርነት ይኖረዋል፡፡
እብራውያን 410-11 ላይ ‹‹ስለዚህ ያንን ትውልድ ተቆጥቼ -ዘወትር በልባቸው ይስታሉ መንገዴን ግን አላወቁም አልሁ እንዲሁ -ወደ እረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ፡፡››የሚል ቃል ገራሚ ቃል አለ፡፡የጌታችን የልብ ሀሳብ ለህይወታችን መልካም ሆኖ ሳለ ብዙ ጊዜ ልባችን ሲያፈነግጥና፣ሳናስቸግረው እና ስንጋደድ እራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ማለትም የብዙዎቻችን ህይወት ከዚች ሴት ምላሽ ጋር በሚገባ ይመሳሰላል፡፡
ዮሀንስ 1010 ላይ ‹‹ እኔ ህይወት እንዲሆናችሁ እንዲበዛላችሁ መጣሁ›› እንደሚል ህይወቱ በዝቶልን ለሌሎች እንድንተርፍ ነው የጌታ ዋና የልብ ሀሳብ!
ግን እንደምታዘበው ከኔም ሆነ ከብዙዎች ክርስትያኖች በቂ ምላሽ እያገኘ አይደለም፡፡ብዙ ነገሮችን በቀለም ደረጃ እናውቃለን፡፡ግን መጠየቅ ያለበት ጥያቄ፡-
ጌታን በሚገባ በግል እናውቀዋለን ወይ ?
ህይወቱ በዝቶልናል ወይ ?እረክተናል ወይ ?
ከዚህ የተነሳ ሰዎች በእኛ ህይወት ክርስቶስን እያዩ ነው ወይ ?
እነዚህ ከላይ ያሉት ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ በህይወታችን ምላሽ እንዲያገኙ ወደ ጌታ በሚገባ መቅረብ አለብን፡፡ሀያዋርያው ያእቆብ ‹‹ወደ እግዚአብሄር ቅረቡ እርሱም ይቀርባችኋል›› እንደሚል በእኛ በኩል የምንወስዳቸው የመቅረብ ውሳኔዎችና እውነተኛ ተግባሮች በህይወታችን ትልቅ ፍሬ እንድናፈራ ያደርጉናል፡፡
ወደ ጌታ በቀረብን ቁጥር በመንፈሱ እየታደስንና ከፍ ያሉ እይታዎችን እያገኘንና ግንኙነታችን እየጠለቀ ይመጣል፡፡በዚህ በጠለቀ ግንኙነትም መንፈሳዊ እርካታ ወደ ህይወታችን ይመጣል፡፡ይህ እርካታ ደግሞ ምድራዊና  ረብ ለሌላቸው ነገሮች እንዳናጎነብስና እንዳንሰጥ ሀይል ይሆነናል፡፡
የጌታችን ለኛ ያለው አላማ በመሀልይ 51ላይ እንደተጠቀሰው እስክንረካ ድረስ ከመንፈሱ እንድንጠጣ ነው፡፡ለዚህ ቃል ማረጋገጫ የሚሆን ደግሞ ዮሀ 737 ላይ ‹‹ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፡፡በእኔ የሚያምን መጸሀፍ እንዳለ የህይወት ውሀ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል››የሚል ድንቅ ግብዣን እናገኛለን፡፡ይህንንም ኢየሱስ የተናገረው ታላቁ የአይሁዶች የዳስ በአል ሊያልቅ ትንሽ ጊዜ ሲቀረው ሲሆን ሰው ሁሉ በግብዣ ተንበሽብሾ ከከረመ በኋላ በመሆኑ በሌላ መንገድ የቆያችሁበት ግብዣ ውስጣዊ እና ዘለቄታዊ እርካታ የለውም ማለቱ ይመስላል፡፡አዎ በእርግጠኝነት በየትኛውም ድል ያለ ግብዣ ላይ ብንገኝ ውስጣዊ የሆነና ዘለቄታ ያለው እርካታ አናገኝም ለጊዜው ብንሸነገልም፡፡
በዚህ በዮሀንስ ወንጌል ላይ ባለው ቃል መሰረት ምን ይሁን ምን የሰው ልጅ ውስጥ የሆነ ‹‹ጥማት›› እንዳለ ቃሉ ይጠቁመናል፡፡ይህንን ‹‹ጥማት››ደግሞ በተለያየ ነገር ለማርካት የሰው ልጅ የማያደርገው ነገር የለም፡፡ነገር ግን የሰው ልጅ ወደ ነፍሱ እረኛና ጠባቂ በሚገባ ካልተመለሰ በስተቀር በዚህ ምድር ነፍሱን የሚያረካ ከጥማትና ከመቅበዝበዝ የሚያወጣና የሚገላግለው ምንም ነገር የለም፡፡
ኢሳ 551-2 ላይ ‹‹እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውሀ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ፡፡ገንዘብን እንጀራ ላይደለ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ለምን ትመዝናላችሁ አድምጡኝ በረከትንም ብሉ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው››የሚል ሌላ እጅግ የሚገርም ግብዣን እናገኛለን፡፡በተለያየ ምድራዊ በሆነና ከሰአታት በኋላ በሚበን ደስታ መሳይ ነገር ጊዜያችሁን አታጥፉ ይልቁንም ‹‹ልባችሁ በጮማ ደስ ይበለው›› ነው ቃሉ የሚለን፡፡‹‹ጮማ›› የሚለው ቃል በዚህ አውድ መሰረት ከእግዚአብሄር ቃልና መንፈስ ጋር ግንኙነታችን ሲጠልቅ የምናገኘውን በረከት ነው የሚወክለው፡፡ሁልጊዜ ይህንን ቃል ሳነብ ከባድ መንፈሳዊ ጉጉትን ይፈጥርብኛልና እወደዋለሁ፡፡ይህ በረከት ደግሞ ልባችንን ከምናስበው በላይ እጅግ ደስ ያሰኘዋል፡፡ደስታው ደግሞ በሰአታት የሚበን ሳይሆን እያደር የሚግልና እየበረከተ የሚሄድ ነው፡፡ይህንን በህይወቴ ስላየሁ ህያው ምስክር ነኝ፡፡ይህ ነው እግዚአብሄር ለእኛ ያለው አላማና ፍቃድ!
ስለዚህ ያለምንም ማወላወልና ማመንታት ወደ ጸጋው ዙፋን መጥተን በፊቱ በቂ ጊዜን በመወሰንና በመጨከን እናሳልፍ፡፡ከእግዚአብሄርም ቃል ጋርም በቂ ጊዜ ይኑረን፡፡ያኔ አስደናቂ የሆነ ህይወት ውስጥ እራሳችንን እናገኘዋለን!

ጎበዝ እንገኝለት


እግዚአብሄር ሊባርከንና ሊያስደንቀን ይፈልጋል፡፡ግን ጌታ ከእኛ በቂ ጊዜን ይፈልጋል፡፡ብዙ ጽሞና፣ብዙ ፊቱን መፈለግ፣ብዙ መቃተት እና በእግሩ ስር መሆን ያስፈልገናል፡፡መዝ 8920-21 ስንገኝለት ስላለ በረከት ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት
ቅዱሱን ዘይትም ቀባሁት
እጄም ትረዳዋለች
ክንዴም ታጸናዋለች
ባጭሩ ሶስት በአእምሮ ለመረዳት የሚከብዱ ድንቅ በረከቶችን እናገኛለን፡-
1.የመንፈስ ቅዱስ ቅባት በሀይል ወደ ህይወታችን ይመጣል
2.እርዳታውና ሞገሱ በህይወታችን በሚታይ ሁኔታ ይበዛል
3.መረጋጋትና ጽናት የህይወታችን መገለጫ ይሆናል
እነዚህ ከላይ ያሉ በረከቶች በነካ ነካ ጸሎት አይመጡም ፡፡የጸሎት ጀግኖች መሆን አለብን፤በጸጋው ዙፋን ፊት አብዝተን መሆን ይጠበቅብናል፡፡እንደ ጳውሎስ እና እንደ ኤጳፍራ የጸሎት ሰዎች መሆን ያስፈልገናል፡፡ያኔ ለብዙ ሰዎች የምንጠቅም የጌታ ባሪያና የክብር እቃ እንሆናለን፡፡ጌታ ሆይ ያለ መታከት ፊትህን እንድንፈልግ እርዳን!

ጌታ ሆይ ተገለጥ

እባክህ ጌታ ሆይ
       ስማን እሺ በለን
እሳትህን ጣለው በመካከላችን
በረዶው ሰለቸን ከቦን በዙሪያችን
በግምባር ተደፍተው
              በውነት ያመለኩህ
ክብርህን አይተው ነው
               የተዋረዱልህ
ስለዚህ ተገለጥ
            ተገኝተህ ገላግለን
መሮናል እሳቱ ሰዎች የለኮሱት
            ቅንጣትም አልበጀን !


መዝ 85፡6
<<አቤቱ ትመለሳለህ ታድነንማለህ
ህዝብህም በአንተ ደስ ይላቸዋል>>


No comments:

Post a Comment