Wednesday, August 21, 2013

በመንፈስ መጸለይ




በጭንቀትና በሀዘን ውስጥ ወይም ግራ በሚገባ ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንዴት እንደምንጸልይ አናውቅም፡፡አንዳንዴም የምናወጣቸው ቃላቶች እና አእምሮአችን ልንጸልይ የምንፈልገውን መግለጽ ሊያቅታቸው ይችላል፡፡ቃላት ጸሎታችንን መግለጽ ሲያቅተው በመንፈስ ቅዱስ ላይ በመደገፍ እርሱ በውስጣችን እንዲቃትት ብንፈቅድለት ከፍ ያለ ጸሎት መጸለይ እንችላለን፡፡ሮሜ 26-27
ብዙ የስነ-መለኮት አዋቂዎች ሀና በመንፈስ ትጸልይ እንደነበረ ይስማማሉ፡፡(1ሳሙ 112-16)የሀና ከንፈሯ ይንቀሳቀስ ነበረ ቢሆንም ነገር ግን ድምጽዋ አይሰማም ነበር፡፡ስለዚህ ታላቁ የእግዚአብሄር ሰው ኤሊ ተሳስቶ ጠጥታ የሰከረች መሰለው፡፡ሀና ከበድ ባለ ጭንቀት ውስጥ ስለ ነበረች በመንፈስ ትቃትት ነበር፡፡ሃና በአራቱም ማእዘን እየደረሰባት ካለው ፈተና የተነሳ ምሬት ውስጥ ነበረች፡፡በሴትነቷ እና በሚስትነት ማንነቷ ላይ የተነጣጠረ አደጋ ስለነበረ መከራዋ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ስለዚህም እግዚአብሄርን በጽኑ ፈለገችው፡፡በመንፈስ ብርቱ ጸሎትን ጸለየች፡፡ሳትታክት በጌታ ፊት ተጋች፡፡ስለዚህም በዘመኑ ብርቱ የነበረ ሳሙኤልን ወለደች፡፡
እኛም አዳጋች ነገር ሲገጥመን ወደ ጸጋው ዙፋን መጥተን በመንፈስ ብንጸልይና ረዘም ላሉ ሰአታት ብንቃትት ጸሎቱ በቀጥታ ከእግዚአብሄር ጋር ስለሚያገናኘን እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ያለ ጸሎትን እንጸልያለን፡፡ችግራችንም በእግዚአብሄር ጊዜ በአስደናቂ ሁኔታ ይንከባለላል፡፡
እግዚአብሄር ሆይ እባክህ የጸሎትን ሚስጥር ግለጥልን!


     ልዩ ነህ

ውበትህ ልዩ ነው
    የለም የሚመስልህ
አሰራርህ ልዩ
   ብዙ ነው ጥበብህ
ሰምቼ ነበረ ብዙ በጆሮዬ
አይኔ አይታሀለች
      የኔም በተራዬ
ታዲያ ለማሞገስ
ቃላት አጣሁና
      አንተ ለማወደስ
ዝም ብዬ ብዳክር
የሚመጥን ሀሳብ
    ቢጠፋኝ ብቸገር
እንዲያው ሁሉን ጥዬ
እጆቼን አነሳሁ
    ፊቴን አንጋጥጬ
    ይገባሃል ብዬ!

የምጥ ጸሎት (travailing prayer)

የምጥ ጸሎት በተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ምሪቶችና መረዳቶች የሚከናወን ጸሎት ሲሆን ብዙ ጊዜ ከፊት ለፊት ተግዳሮቶች፣መከራዎች እና ልብን የሚሰብሩ ክስተቶች በህይወታችን ሲያልፉ ልንጸልየው እንችላለን፡፡
የምጥ ጸሎት 5 ደቂቃ ብቻ ሊጸለይ ይችላል ወይም ረዘም ላሉ ቀናት ሊጸለይ ይችላል፡፡አብዛኛውን ጊዜ የጸሎት ሸክሙ መንፈሳችን ውስጥ እስካለ ድረስ አያሳርፈንም፡፡እኛም መለቀቅ እስኪመጣ አናቆመውም፡፡
ፍሬውና በረከቱ ደስ ቢያሰኝም የምጥ ጸሎት ህመም አለው፡፡ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳያስ ከባድና አስደንጋጭ መንፈሳዊ መልእክት ሰምቶ የጸለየው የምጥ ጸሎት ያስደንቀኛል፡፡እርሱም ኢሳ 218 ላይ ይገኛል፡-‹‹…ስለዚህ ወገቤ ህመም ተሞላ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፤ከህመሜ የተነሳ አላይም፡፡ልቤ ተንበደበደ ድንጋጤ አስፈራኝ ተስፋ ያደረግሁትመ ድንግዝግዝታ መንቀጥቀጥ ሆነብኝ፡፡›› ብሎ ይገልጸዋል፡፡የሚገርም ጸሎት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች እንዲህ አይነትን ጸሎት ሲጸልዩ በጉልበታቸው ተንበርክከው ልክ እንደምትወልድ ሴት እያማጡና እየቃተቱ ለብዙ ሰአታት ይጸልያሉ፡፡እንዲህ አይነት ጸሎት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በጠለቀ መንገድ በመዋሀድ የሚጸለይ ጸሎት ስለሆነ ብዙ ድንቅ ነገሮችን እናይበታለን፡፡
ለብዙ ለተለያዩ ጉዳዮች ይህንን ጸሎት ልንጸልይ እንችላለን ለምሳሌ ለነፍሶች መዳን፣ለቤ/ ማደግ፣ከተለያዩ አደገኛ ሁኔታዎች ለማምለጥ ፣ከምንታገልባቸው ሀጢያቶች ለመውጣት ወዘተ፡፡
ከእየሱስ ቀጥሎ እንደሀዋርያው ጳውሎስ ለቤ/ መወለድና ማደግ በእኩል ሁኔታ ያማጠ ሰው በምድር ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ጳውሎስ ገላ 419 ላይ ስለዚህ አይነት ጸሎቱ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-‹‹ልጆቼ ሆይ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሳል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል፡፡››አያስቀናም! ራሱን የካደና የክርስቶስ ልብ የነበረው ሰው ነበር፡፡በዚህ አይነት ጸሎት ውሎ የሚያድር የነበረ ሰው ይመስለኛል፡፡ድንቅ አገልግሎት!እባክህ ጌታ ሆይ በእንደዚህ አይነት ጸሎት ባርከን!
እራሳችንን ለዚህ ጸሎት በሰጠንበት ልክ ይህ አይነት ጸሎት እየሰፋና እየጠለቀ ማቆሚያ ወደሌለው መንፈሳዊ ልምምድ ውስጥ ስለምንገባ ለብዙ ሰዎች በረከት እንሆናለን፡፡
ዮሀንስ 1620-22 ላይ ያለው ቃል እነዚያ 120 ክርስትያኖች እየሱስ ካረገ በኋላ በሰገነት(upper room) ላይ ወጥተው ስላከናወኑት የጸሎት ምጥ የተነገረ ትንቢታዊ ቃል እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡እንዲህ ይላል፡-እናንተ ታለቅሳላችሁ ሙሾም(ከበድ ያለ ለቅሶ ነው) ታወጣላችሁእናንተም ታዝናላችሁ ነገር ግን ሀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል….እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ ነገር ግን እንደገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል…››
መንፈስ ቅዱስ ያሳየኝን ኡደት ላስቀምጥ -
የምጥ ጸሎት----------›እርሱ የእንደገና አምላክ ነውና ያየናል ------------›ልባችንም ደስ ይለዋል(ደስ የሚለውን የእንግሊዝኛ መጽሀፍ ቅዱሶች ከመጠን ያለፈ ደስታ እንደሆነ ለመግለጥ exceeding joy ብለው ይገልጹታል)-------------------›ከጀመርነው ከፍ ወዳለ የምጥ ጸሎት ውስጥ እንገባለን---------›የእንደገና አምላክ ያየናል---------------›ይቀጥላል
የምናሳልፈው ጊዜና ጉዳይ በጣም ከባድና የማያልፍ እስኪመስል ሊያስምጠንና ሊያስለቅሰን ይችላል፡፡ነገር ግን የእንደገና አምላክ በጉብኝቱ ሲመጣ ሶስት ነገር ነው የሚሆነው፡-
  •   እርሱ እንደገና ያየናል
  •   እኛም በሚዳሰስና ግር በማይል መልኩ እናየዋለን
  •   ምስክርነታችንም ግሩምና ጠንካራ ይሆናል
እዚህ ዮሀንስ ላይ የተጠቀሰው ቃል መጨረሻ ላይ ያለው ተስፋ ነው የሚያስደንቀኝ እንዲህ ይላል፡-‹‹ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም፡፡››እንግሊዝኛው እንዲህ ይለዋል ‹‹no one rob you of that joy>>በቀጥታ ሲተረጎም ማንም ይህንን ደስታ ሊዘርፋችሁ ወይም ሊገፋችሁ አይችልም ማለቱ ነው፡፡ለምን መሰላችሁ እውነተኛ፣ሀይለኛ፣የጠለቀ፣በመንፈስ የጋየና ከውስጥ ከጥልቁ የተቀዳ ደስታ ስለሆነ ነው፡፡ጌታ ሆይ በእንደዚህ አይነት ጸሎት ባርከን!
                   


    

No comments:

Post a Comment